ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል 109 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማቅመም ሰብል ተሸፍኗል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 06/2015  በደቡብ ክልል 109 ሺህ ሄክታር መሬት በቅመማቅመም ሰብል መሸፈኑን የክልሉ ቡናና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ገለጸ።


የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን በቅመማቅመም ልማትና ምርት ዝግጅት የልምድ ልውውጥ መድረክ በደቡብ ክልል ሥልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ በቅመማቅመም ልማት ላይ የሚሰሩ የክልል ተወካዮች፣ አርሶ አደሮች፣ የቅመማቅመም ምርትና ግብይት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዘርፍ ባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊዎች ናቸው።



በወራቤ ከተማ ዙሪያ አንሼ ቤሶ ቀበሌ በኩታገጠም የለማ የጥብስ ቅጠል (ሮዝመሪ) ማሳም ተጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ ቅመማቅመም በአግባቡ ከተሰራበት፣ ከቡና ያልተናነሰ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ገልፀዋል።

የቅመማቅመም ምርት የልምድ ልውውጥ ገበያ ለማሳለጥና በጋራ ለመሥራት ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገርም የባህል ልውውጥ የሚደረግበት በመሆኑ፣ የልምምድ ልውውጥ መድረኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በቅመማቅመም ምርቶች ረገድ በሥልጤ ዞን ሮዝመሪና ዝንጅብል በስፋት እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በሽታዎችን በባህላዊ ዘዴ የመከላከል ባህልን የበርበሬ አምራቾች ሊቀስሙት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የደቡብ ክልል የቡና እና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ከድር፤ በክልሉ ቡናና ቅመማቅመም በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሬን  ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በቅመማቅመም ረገድ በርበሬ፣ ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣ አሪቲና ሌሎች በርካታ ዓይነት ቅመማቅመም በ109 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ነው።

በ 2014 የምርት ዘመን ከ124 ሺህ ቶን በላይ የቅመማቅመም ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አስታውሰው፤ በተያዘው ምርት ዘመንም ባለፉት አምስት ወራት ከ52 ሺህ ቶን በላይ ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልፀዋል።

በክልሉ ከ6ሺህ 900 በላይ ሄክታር መሬት በሮዝመሪ ምርት የለማ መሆኑን ገልፀዋል።

በምርምር ማዕከላት እየተደገፈ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሥልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዓሊ ከድር በበኩላቸው፤ ከግብርና ምርቶች መካከል በዞኑ  ባለፈው በጀት ዓመት በሮዝመሪ ምርት ከ730 ሺህ ዶላር በላይ ተገኝቷል።

የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ግብዓቶችን ማማሏትና የግብይት ተግዳሮቶችን መቅረፍ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም