ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት የሚስተካከል ገቢ በመሰብሰብ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ይሰራል--ገቢዎች ሚኒስቴር

42

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 6/2015 በአገሪቱ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት የሚስተካከል ገቢ በታማኝነት በመሰብሰብ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በድሬዳዋ ታማኝና አርአያ ለሆኑ 50 ግብር ከፋዮች እና 12 ሴክተሮች የዋንጫና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ዕውቅናና ሽልማቱ ግብርን በታማኝነት የማይከፍሉት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲመጡና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሃብት የሚስተካከል ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

መንግስት የአገር ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ሀብት ያህል ገቢ ለመሰብሰብ የተለያዩ ዘመናዊ አሠራሮች፣ አደረጃጀቶች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለግብር ሥርዓቱ የሚገዛና አገርን ለመገንባት በታማኝነት ግብርን የሚከፍል ማህበረሰብ የመፍጠር ሥራ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

"እውቅና የተሰጣቸው የድሬዳዋ ታማኝ ግብር ከፋዮች ታማኝና ከማጭበርበር ነፃ የሆኑ ሌሎች ግብር ከፋዮች በብዛት እንዲፈሩ በማገዝ የድሬዳዋ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ሃብት የሚስተካከል ገቢ እንዲሰበሰብ መትጋት አለባቸው" ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፣ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ የሚሰበሰበው ገቢ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት ያህል ገቢ ለመሰብሰብ የተለያዩ ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋትና ዘርፉን ከሙስናና ሌብነት ለመከላከል አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ግልፅ፣ ተደራሽና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር በመዘርጋት ታማኝ ግብር ከፋዮች እንዲበዙ ከመቼውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን" ሲሉም አረጋግጠዋል።

"በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በከፍተኛ ታማኝነት የሚጠበቅባችሁን አገራዊ ግብር የመክፈል ኃላፊነታቸሁን በመወጣታችሁ ለሁሉም ግብር ከፋይ አርአያ ትሆናላችሁ" ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጠብ 5 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።

ባለፈው ዓመትም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡

እንደ አቶ አብዱልሰላም ገለጻ ዘንድሮ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ካለፈው ሐምሌ 1 ቀን 2014 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ባሉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በድሬዳዋ ለ3ኛ ጊዜ ለታማኝ ግብር ከፋዮችና ሴክተሮች በተሰጠው ዕውቅናና ሽልማት መርሃ-ግብር ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትሂያ አደን የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ቱሉ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም