ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በቡራዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች 13 ሚሊዮን ብር ደገፉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በቡራዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች 13 ሚሊዮን ብር ደገፉ
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው "ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውን መብት" በቡራዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች 13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አስተባባሪዎች ለተጎጂዎች ያሰባሰቡትን ገንዘብ ለብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል። የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አርቲስት ታማኝ በየነ እንዳለው፤ ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውን መብት በኢትዮጵያ ተጎጂዎችን ለመርዳት አስቸጋሪ በሆነበት ወቅትም በተለያዩ ተቋማት ስም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። የተደረገው ድጋፍ በቡራዩ ከተማ በኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ግድያ፣ እንግልትና ማፈናቀል ባያካክስም ዜጎች ዘመድና ወገን አለን ብለው ተስፋ እንዲሰንቁ ያግዛቸዋል ብሏል። በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተሰበሰበው 13 ሚሊዮን ብር በአግባቡ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ኮሚቴው ከመንግስት ጋር መርሃ-ግብር እያወጣ ይቆጣጠራል ብሏል። ተጎጂዎች ከደረሰባቸው ችግር አገግመው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲጀምሩ የእርዳታውን ሂደት ሁሉም በኃላፊነት ስሜት መከታተል እንዳለበት ገልጿል። በቀጣይም ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት ለመከላከል እርስበርስ ቃላት ከመወራወር መቆጠብ ይገባል ብሏል። "ይህ ባለፉት ዓመታት በፖለቲከኞች የተፈጠረውን የዘር ፖለቲካ ለማጥፋት ዛሬም ፖለቲከኞችን ከመጠበቅ እኛም ገብተን መታገል ይኖርብናል" ብሏል። የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለተጎጂዎች ያደረጉት ድጋፍ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በእነዚህ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የተሰበሰበው ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ኮሚሽኑ በየዘርፉ ካለው የመንግስት መዋቅር ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል። እስካሁን የተሰባሰበው ገንዘብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን መሆኑን የገለጸው ኮሚቴው በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎች መርዳት ከፈለጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000258694736 ገቢ ማድረግ ይችላሉ ብሏል።