በግጭትና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተዳረጉ ሴቶችና ህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የተመድ ስነ-ህዝብ ፈንድ - ኢዜአ አማርኛ
በግጭትና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተዳረጉ ሴቶችና ህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የተመድ ስነ-ህዝብ ፈንድ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 06/2015 በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭትና ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተዳረጉ ሴቶችና ህፃናት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የስነ-ህዝብ ፈንድ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች፣ በአየር ፀባይ ለውጥ ችግርና በአገር ውስጥ መፈናቀል በርካታ ሰዎች ለተለያዩ ሰብዓዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስነ-ህዝብ ፈንድ የሰብዓዊ እርዳታ ፕሮግራም አስተባባሪ ጀምስ ኦካራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭትና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ በተለይ ሴቶችና ህፃናት የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተባበሩት መንግሥታት የስነ-ሰብ ፈንድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በግጭትና በድርቅ ሳቢያ ተጎጂ ለሆኑ በትግራይ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሌሎችም አካባቢዎች ከ24 ሺህ በላይ ሴቶች የወሊድ፣ የድህረ-ወሊድ፣ የእናቶችና የህፃናት እንክብካቤ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ለአማራና አፋር ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ጣቢያዎች 30 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ መብራቶች ሲለግስ የሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ ለአራቱ ክልሎች ዘጠኝ አምቡላንሶችንና የሕክምና ግብአቶችን ማድረሱንም ተናግረዋል።
ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተሟላ የሕክምና ቡድን የያዙ አራት ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን በሰሜኑ ግጭት በተጎዱ አካባቢዎች በማቋቋም ድጋፍ እየሰጠ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በተያዘው ዓመት ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩና በአማራ፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች የእናቶችንና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጤና አገልግሎት ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።
ከችግሩ ስፋት አኳያ ገና በርካታ ሥራዎች መከናወን አለባቸው ያሉት አስተባባሪው ሌሎች አጋር አካላትም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።