የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የእግር ኳስ ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የእግር ኳስ ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የእግር ኳስ ዋንጫ ዛሬ መከላከያና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያደርጉት ጨዋታ ፍጻሜውን ያገኛል። ጨዋታው ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ሠዓት በሀዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል። በ2010 ዓ.ም መጠናቀቀ የነበረበት ይህ የጥሎ ማለፍ የእግር ኳስ ዋንጫ የተወሰኑ ጨዋታዎችን በዚህ ዓመት በማከናወን ፍጻሜው ላይ ደርሷል። የዛሬው አሸናፊ ክለብ በዚህ ዓመት በሚደረገው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የእግር ኳስ ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ ይካፈላል። በአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድሮች በተለይም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ረጅም ጊዜ የመሳተፍ ልምድ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2010 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ጅማ አባጅፋር በመውሰዱ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ ውጭ ሆኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ዓመት በአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ ያለው ዕድል የዛሬውን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ማሸነፍ ይሆናል።ተጋጣሚው መከላከያም በጥሎ ማለፉ ዋንጫ በማንሳት ልምድ ያለው ክለብ ነው። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ መከላከያ ሶስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ መሳተፍ ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ ከተደራጀ በኋላ አራት ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።