ቀጥታ፡

ከሠላም ሥምምነቱ በኋላ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ፍላጎት እያሳዩ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 5/2015 በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ተከትሎ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሠማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ዛሬ ከአጋር አካላት ጋር ተወያይቷል።

ኮሚሽነር ኢንጅነር ሌሊሴ ነሚ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ኢንቨስትመንት አመራጮችና እድሎች አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።

አጋር አካላት በኢትዮጵያ አሁን የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅመው የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከማድረግ አኳያ በጋራ መሥራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች አንስተዋል።

ከውይይቱ በኋላ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሰላም ስምምነቱ  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስተመንት መስክ ለመሰማራት ከወዲሁ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያና አፍሪካ ተወካይ ኢሌኒ ካይሩ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ መረጋጋት ለኢንቨስትመንት ምቹ እድል ይጥራል ብለዋል።

በዚህ መሰረት የሰላም ስምምነቱ ለኢንቨስትመንቱ አንድ ምዕራፍ የከፈተ በመሆኑ ይህን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ጂ አይ ዜድ/ በኢትዮጵያ የዘላቂ ኢንዱስትሪ ክላስተር መርሃ ግብር ሃላፊ የሆኑት አና ዋልድማን፤ ሰላምና መረጋጋት ኢንቨስትመንት ለመሳብ ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ድርጅታቸው ጂ አይ ዜድ ኢትዮጵያ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም