ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞቹንና የአካባቢውን ነዋሪዎች በጓሮ አትክልት ተጠቃሚ አደረገ

አዲስ አበባ  /ኢዜአ/ ታህሳስ 5/2015 የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰራተኞቹንና የአካባቢው ነዋሪዎች በተቋሙ ቅጥር ግቢ የጓሮ አትክልት እንዲያለሙና እንዲጠቀሙ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አስፋ፣ በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄንሪክና የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክርስቲያንሰን በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ በስዊድን የልማት ድርጅት (ሲዳ) ድጋፍ የሚለማው የጓሮ አትክልት ጎብኝተዋል።

በዚህም በተቋሙ ቅጥር ግቢ በአነስተኛ ቦታ የተለያዩ ጓሮ አትክልቶችን በማልማት 100 የሚጠጉ የተቋሙን ሰራተኞችና በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሚኒስቴሩ ሰራተኞችና በአካባቢው የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ምርቱን በዝቅተኛ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ ሆነዋል።

በሲዳ የ14 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኘው ፕሮጀክት የጓሮ አትክልት፣ የዶሮና የአሳ እርባታ ያከተተ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት በሚኖሩበት ቦታ የጓሮ አትክልት በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄንሪክ በበኩላቸው የስዊድን መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ሳህነ ጽጌና ወይዘሮ ሰሚራ ሃይሉ

በበኩላቸው በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉና በገቢም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጠቁመዋል።

በጓሮ አትክልት ፕሮጀክቱ ከ80 በመቶ በላይ ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የፋርም አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሸዊት አማኑኤል በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ዜጎች በትንሽ ቦታ ከፍ ያለ ምርት በማምረት ትልቅ ውጤት ማግኘት እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በጓሮ አትልክት ማምረት ላይ የተሳተፉትና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩት ተጠቃሚዎች ፕሮጀክቱ ኑሯቸውን እንዳሻሻለላቸው አረጋግጠዋል።

ከስራቸው ጎን ለጎን በማኅበር በመደራጀት እስከ 70 ሺህ ብር መቆጠብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም