የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 5/2015 የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች የሚውል 745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ በተለይም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና የጎርፍ አደጋ አስተዳደር የተመለከቱ ሁለት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
ባንኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከኮቪድ 19፣ ከአየር ጸባይ ለውጥና ከግጭት ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ጠቅሷል።
ይህ ደግሞ አስፈላጊ የተባሉ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች ማድረጉን እንዲሁ።
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ነው የተጠቀሰው።
አሁን አሁን ስጋት እየሆነ የመጣውን የጎርፍ አደጋ የእርሻ መሬቶችንና የእንስሳት ሃብቶችን በማውደም ኢትዮጵያን ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳሳጣት የባንኩ ሪፖርት ያሳያል።
ባንኩ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ይረዳል ያለውንና ለሁለት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የሚውል የ745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ዛሬ አጽድቋል።
ፕሮግራሞቹ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ፕሮጀክትና የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቶች ሲሆኑ እንደ ቅድም ተከለተላቸው 445 ሚሊየን ዶላርና 300 ሚሊዮን ዶላር እንደተመደበላቸው ተጠቁሟል።
የባንኩ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ተጠሪ ኦስማኔ ዲኦን ድጋፉ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉና ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
የጤና ፕሮጀክቱ 22 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የታመነበት ሲሆን የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቱ በበኩሉ በአዋሽ ኦሞና በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የሚኖሩ 34 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።