ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ለልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች ስኬታማነት የዘርፉ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 5 ቀን 2015 በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የዘርፉ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ እያሱ ሳላ በክልሉ ልማትን፣ መልካም አስተዳደርንና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነት ላይ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑ የፌዴራል የሚዲያ፣ የህግ፣ የዴሞክራሲና ሌሎች  ተቋማት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት እቅዳቸውን ለመፈጸም እያደረጉት ያሉት ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በክልሉ ላለው ከ370 ሺህ በላይ ስደተኞች እየሰጠ ያለው የሰብዓዊ አገልግሎትና ጥበቃ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ተቋማቱን በማብቃት፣ በድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል።

ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ሙሉነሽ ላሞሬ በበኩላቸው፤ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ሁሉም የህግ ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት የዓመቱን እቅዳቸውን ለማሳካት ብርቱ ጥረት እያደረጉ እንደሆኑ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም  በተወሰኑ ተቋማት የሰው ኃይል፣ የግብዓትና ምቹ የስራ ቦታን ከመፍጠር አኳያ ድጋፍና ክትትል የሚሹ  መኖራቸው አመልክተዋል።

ተቋማቱ በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀምና ተደራሽነትን በማስፋት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከክልሉ መንግስት ጋር የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሰራሮች ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የውልሰው ንጉሴ፤ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በስደተኞች አያያዝና ሰብዓዊ አገልግሎት ዙሪያ የተሰጣቸው ግብረ-መልስ በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአካባቢውን ማህበረሰብና የስደተኞችን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በአካባቢ ደን ልማትና ጥበቃ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ በተሰጣቸው ግብረ-መልስ መሰረት ጠንክረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በክልሉ በነበራቸው ቆይታ የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንና ሌሎች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን በመዘዋወር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም