ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፊርማው ያረፈበትን ማልያ በመላክ ይቅርታ የጠየቃቸው የዛሬው የሞሮኮና ፈረንሳይ ጨዋታ የመሐል ሜዳ ዳኛ አርቱሮ ራሞስ ፓላዙዌሎስ ማናቸው?

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 5/2015 በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ ተጠባቂው የሞሮኮና የፈረንሳይ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰአት በአል በይት ስታዲየም ይካሄዳል።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከሜክሲኮ በዋና ዳኝነት እንዲያጫውቱ የመረጠው አንድ ዳኛ ብቻ ነው።

ብቸኛው ተመራጭ የ38 ዓመቱ ሴዛር አርቱሮ ራሞስ ፓላዙዌሎስ ይባላሉ።

ሴዛር ራሞስ እ.አ.አ ታህሳስ 15/1983 በሜክሲኮ ሲናሎአ ግዛት በምትገኘው ትልቋ ከተማ ኩሊካን ሮሳሌስ ከተማ ተወለዱ።

የዳኝነት ቆይታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ ጥቅምት 28 /በ2006 በሜክሲኮ ‘አሴንሶ ኤምኤክስ’ እየተባለ በሚጠራው የሜክሲኮ ሁለተኛ ሊግ ዛካቴፔች ከሳንቶስ ላጉና ባደረጉት ጨዋታ ነው።

በዋናው የሜክሲኮ የእግር ኳስ ሊግ እ.አ.አ ጥር 15/2011 ሳን ሉዊስ ከፑዌብላ ያደረጉትን ጨዋታ አራተኛ ዳኛ በመሆን በረዳትነት መርተዋል።

ሴዛር ራሞስ እ.አ.አ 2011 ማብቂያ በሜክሲኮ የእግር ኳስ ሊግ በሞንቴሬይ እና ቲዩዋን ክለቦች ጨዋታ በሊጉ በዋና ዳኝነት የመሩት የመጀመሪያ ጨዋታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።

ፈርናንዶ አርቼ ሴዛር ራሞስ በሜክሲኮ ሊግ ቢጫ ካርድ የመዘዙበት የመጀመሪያው ተጫዋች ሲሆን በ15 ደቂቃ ሁለት ቢጫ በመስጠት ከሜዳ ያሰናበቱት ማሪያኖ ትሩይሎ ደግሞ በሊጉ የመጀመሪያ ቀይ ካርድ ያሳዩት ተጫዋች ነው።

ሴዛር ራሞስ እ.አ.አ በ2014 የፊፋ ዓለም አቀፍ ዳኛ ሆኑ።

እ.አ.አ ታህሳስ 16/2017 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዛይድ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም በተካሄደው የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ በክርስቲያኖ ሮናልዶ ብቸኛ ግብ የብራዚሉ ግሬሚዮን 1 ለ 0 ያሸነፈበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርተዋል።

በ2017 በኮሪያ ሪፐብሊክ አዘጋጅነት በተካሄደው 21ኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ኡራጓይ ፖርቹጋልን ያሸነፈችበትን ጨምሮ ሶስት ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት አጫውተዋል።

የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ እና የካሪቢያን እግር ኳስ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኮንካካፍ) እና የእስያ እግር ኳስ ባደረጉት የዳኞች ልውውጥ ፕሮግራም ሴዛር ራሞስ እ.አ.አ 2019 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው 17ኛው የእስያ ካፕ አራት ጨዋታዎችን መርተዋል።

እንደ ኳታሩ ሁሉ ሴዛር ራሞስ ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ ባሰናዳችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እንዲያጫወቱ የተመረጡ ብቸኛ ሜክሲኳዊ ዋና ዳኛ ነበሩ።

ብራዚል ከስዊዘርላንድ፣ፖላንድ ከኮሎምቢያ እና ኡራጓይ ከፖርቹጋል ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በመሐል ዳኝነት መርተዋል።

ኡራጓይ ፖርቹጋል 2 ለ 1 ያሸነፍችበት ጨዋታ በጥሎ ማለፉ ዙር የተደረገ እንደነበር አይዘነጋም።

ሴዛር ራሞስ በሁለቱ አገራት ጨዋታ ብቸኛ ቢጫ ካርድ የመዘዙበት ተጫዋች ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነበር።

ሮናልዶ ቢጫውን ካርዱን ያየው የቡድን አጋሩ ሪካርዶ ከሬዝማ ላይ ለተሰራው ጥፋት ዳኛው ለምን ካርድ አልሰጡም? በሚል እሰጣገባ ውስጥ በመግባቱ ነው።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከጨዋታው በኋላ ፊርማው ያረፈበትን ማሊያ ለሴዛር ራሞስ በማበርከት ላሳየው ባህሪይ ይቅርታ ጠይቋል።

ሴዛር ራሞስ በኳታር አስተጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እስከ አሁን አራት ጨዋታዎች በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

በዓለም ዋንጫ አስደናቂ ግስጋሴ እያደረገች ያለቸው አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ በምድብ ስድስት የእግር ኳስ ኃያላኗን 2 ለ 0 በመርታት ዓለምን ጉድ ያሰኝችበትን ጨዋታ የመሩት ሜክሲኳዊው ዳኛ ናቸው።

ራሞስ በጥሎ ማለፍ ዙር ፖርቹጋል ስዊዘርላንድን 6 ለ 1 ስትረታ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት መርተዋል።

በምድብ አራት አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ ከዴንማርክ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ የተለያየችበትን ጨዋታ የመሩት ዋና ዳኛም ነበሩ።

ፊፋ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀውን የሞሮኮና ፈረንሳይ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የ38 ዓመቱ ሜክሲኳዊ ሴዛር አርቱሮ ራሞስ ፓላዙዌሎስ በዋና ዳኝነት እንዲመሩት ኃላፊነት ጥሎባቸዋል።

ሴዛር ራሞስ በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመሩ አራተኛ ሜክሲኳዊ ዳኛ ይሆናሉ።

አንቶኒዮ ማርኩዌዝ ራሚሬዝ፣ ቤኒቶ አርቹንዲያ እና ማርኮ ሮድሪጌዝ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን የመሩ የሜክሲኮ ዳኞች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም