ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 5/2015 ሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን አጠናክሮ በመቀጠል ወገኑን ከህመምና ከሞት ሊታደግ እንደሚገባ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

ይህም ሆኖ ሕብረተሰቡ ደመ የመለገስ ባህሉ በሚፈለገው ደረጃ አድጓል ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸው፤ተሳትፎውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

"ደም በባህሪው የቆይታ ብሎም የመጠቀሚያ ጊዜ በቀናቶች የተገደበ በመሆኑ በአንድ ወቅት ብቻ ከደም ለጋሾች ተሰብስቦ የሚተው ሥራ አይደለም" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለይም ከደም ዓይነቶች መካከል ኦ-ኔጌቲቭ በተወሰኑ ደም ለጋሽ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚገኝ መሆኑ በደም ባንኩ የሚኖረውን የደም ክምችት መጠን አናሳ አድርጎታል ነው ያሉት።

በአገሪቱ በሚገኙ በተለያዩ የጤና ተቋማቶች ላይ በቂ የደም አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል በመደበኛነት ደም የሚለግሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም በመደበኛነት ደም የሚለግሱ በጎፈቃደኛ ዜጎችን በስፋት ለማፍራት ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ከተለያዩ አካላቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የደም አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ተቋሙ  አስፈላጊውን ግብዓቶች በማሟላት አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ደም መለገስ የሰውን ህይወት ከህመምና ከሞት ለመታደግ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሕብረተሰቡ በበጎፈቃደኝነት ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት 190 ሺህ ደም ዩኒት ከሕብረተሰቡ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ 140 ሺህ ደም ዩኒት መሰብሰብ መቻሉን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም