ቀጥታ፡

በክልሉ በ90 ቀናት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 3 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ ወደ ስራ ተገብቷል-ጽህፈት ቤቱ

ሀረር (ኢዜአ) ታህሳስ 5/ቀን 2015  የሀረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ90 ቀናት ውስጥ 3 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ  በክልሉ በገጠርና በከተማ ከሚገኙ ዘጠኝ የወረዳ አመራር አካላት ጋር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰብ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ምክከር አካሂዷል።

የሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊና የታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ  ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበርያ ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ በወቅቱ እንዳሉት የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ወደ እድገት ጎዳና የምታደርገው ሽግግር ማሳያ ነው፡፡

በክልሉ በ2014 በጀት ዓመት የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በነበረው ቆይታ ለግድቡ ግንባታ 15 ሚሊዮን ብር  መሰብሰቡን አስታውሰዋል ።

 ዘንድሮ የክልሉን ማህበረሰብ በማስተባበር  በ90 ቀናት ውስጥ 3 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል ፡፡

ማህበረሰቡ እንደ ካሁን ቀደሙ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ሄኖክ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የሀኪም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቶፊቅ መሃመድ በበኩላቸው "የህዳሴ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች አሻራ ያረፈበት መሆኑን በመግለፅ "የግድቡን ግንባታ እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን" ብለዋል፡፡

በወረዳው በ2014 በጀት ዓመት ከቦንድ ሽያጭ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ያስታወሱት አቶ ቶፊቅ ዘንድሮ የገቢ አሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን   " እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" ያሉት ደግሞ  የአባዲር ወረዳ ምክትል አስተዳደር አቶ መፍቱህ ሸምሱ ናቸው

ከወረዳው ባለፈው ዓመት  ከቦንድ ሽያጭ 800 ሺ ብር መሰብሰቡን አስታውሰው  ዘንድሮ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ450ሺ ብር በላይ  ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም