በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለውጥ መጥቷል

ደሴ (ኢዜአ) ታህሳስ 5/201 በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ በመሰራቱ ለውጥ መምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ገለፁ።

ቢሮው በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራን አስመልክቶ ያዘጋጀው አውደ ጥናት በደሴ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለአማራ ክልል የህልውና ጉዳይ ሆኖ በየዓመቱ እየተከናወነ ነው።

በእዚህም የተራቆቱ፣ ተራራማና ገደላማ አካባቢዎችን በማልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩ ሕይወት እየተቀየረ መሆኑን ገልፀዋል።

በለሙ ተፋሰሶች ላይ ለሥራ እጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው፣ ወጣቶቹ አትክልትና ፍራፍሬ ጭምር በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አርሶ አደሩም በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ ለእንስሳቱ በቂ መኖ እያገኘ መሆኑን ነው ሃላፊው የገለጹት።

የቢሮ ሃላፊው እንዳሉት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችና ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየት በቀጣይ ለማጠናከር እየተሰራ ነው።

በመድረኩ ላይ "ክልላዊ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት የማህበረሰብ አቀፍ ጥናት" በሚል ርዕስ ቢሮው ያስጠናው  ጥናት ለውይይት እንደሚቀርብ ገልጸው፣ የዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀመር አመልክተዋል።

''ወሎ ገደላማና ተራራማ በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በማልማት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እየሰራን ነው'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ናቸው።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ ዞኖች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በቀረበው ጥናት ላይም ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም