ቀጥታ፡

''ድል የተራበ ቡድን ይዘን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው''- የሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 5/2015 ድል የተራበ ቡድን ይዘን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው ሲሉ የሞሮኮው አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ገለጹ።

በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ታሪክ አፍሪካን በመወከል ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ሞሮኮ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ፈረንሳይን ትገጥማለች፡፡

አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ የሞሮኮ ቡድን 'የተጠራጠሩትን ሁሉ አፍ በማዘጋት' ለፍጻሜው ጨዋታ ይደርሳል በማለት በልበ-ሙሉነት ተናግረዋል፡፡

በዓለም ዋንጫ የ92 ዓመት ታሪክ አስደናቂ የተባለውን ጉዞ እያደረገች የምትገኘው ሞሮኮ የአፍሪካ ኩራትነቷን በአደባባይ አስመስክራለች፡፡

የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ ሁለት ወራት በፊት በፈረንሳይ የተወለደውንና የሞሮኮ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመውን ዋሊድ ሬግራጉዊ ከአገሩ ውጪ የሚያዉቁት የእግር ኳስ ወዳጆች ጥቂት ነበሩ፡፡

ብሄራዊ ቡድኑን ከመረከቡ በፊት የአገሩን ክለብ ዋይዳድን በማሰልጠን የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮን ያደረገው ዋዲድ በአለም ዋንጫው የመጨረሻው ግምት የተሰጠውና ልምድ አልባ የተባለው አሰልጣኝ ነበሩ፡፡

የኳስ ቁጥጥር ብቻውን ዋጋ እንደሌለው የሚናገረው ዋሊድ ብዙዎች አጨዋወቱን ቢተቹትም ቡድኑ ያስቆጠራቸውን ጎሎች መነሻ በማድረግ የተቺዎችን አፍ አዘግቷል፣ ስሙንም በአለም እግር ኳስ ታሪክ ላይ ተክሏል፡፡

የሞሮኮው አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ከፈረንሳይ ጋር ስለሚኖራቸው ጨዋታ በሰጡት መግለጫ"ቡድናቸው ድል የተራበ በመሆኑ ግማሽ ፍፃሜ በቂያቸው እንዳልሆነ" ተናግረዋል።

በቡድናቸው ከፍተኛ የአንድነት መንፈስ መኖሩንና ታሪክ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

ተጋጣሚያቸው የወቅቱ ሻምፒዮንና የዓለም ምርጥ ተጫዎቾች ስብስብ ያላት ፈረንሳይ  መሆኗን አስታውሰው ለጨዋታው በአካል፣ በአዕምሮና በታክቲክም መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ከፈረንሳይ ጋር ወሳኝ ጨዋታዋን የምታደርገው ሞሮኮ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኗ አማካኝነት ኳታር ለሚገኙ ደጋፊዎቹ 13 ሺ ትኬት በነፃ ሰጥታለች፡፡

የአገሪቱ አየር መንገድ የሆነው ሮያል ሞሮኮ በበኩሉ ወደ ኳታር 30 በረራዎችን በማከናወንና መንገደኞችን በማጓጓዝ ለዛሬው ጨዋታ እንዲታደሙ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፡፡

በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞሮኮ ጋር የምትጫወተው ፈረንሳይ ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ለፍጻሜ ለመድረስና ዋንጫውን ለማንሳት ያላትን ሁሉ እንደምትሰጥ አሰልጣኟ ዲዲየር ዴሾምፕ ተናግረዋል።

በጨዋታው 20 ሺ የሚጠጉት የሞሮኮ ደጋፊዎች ጩኽት እንደማይበግራቸው የተናገሩት ዲዲየር ዴሻምፕ ሞሮኮ እዚህ የደረሰችው በብቃት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጠንካራ ተከላካይ ያላት ሞሮኮ የያዘቻቸው አጥቂዎች ጥሩ ብቃት ያላቸው በመሆኑ ከሞሮኮ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ቀላል ግምት እንደማይሰጠው አመላክተዋል።

የሞሮኮና ፈረንሳይ ጨዋታ የሚከናወንበትና 68 ሺህ ተመልካች የሚይዘው አል በይት ስታዲየም 20 ሺ በሚጠጉ የሞሮኮ ደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ እንደሚደምቅ ይጠበቃል፡፡

የፈረንሳይና የሞሮኮ አሸናፊ በፍጻሜው ከአርጀቲና ጋር ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም