ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ- አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከመሪዎች ጋር እያደረጉት ያለው የሁለትዮሽ ውይይት በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ትርጉም አለው - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ- አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከመሪዎች ጋር እያደረጉት ያለው የሁለትዮሽ ውይይት በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ትርጉም አለው - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና
አዲስ አበባ /ኢዜአ /ታህሳስ 5/2015 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ- አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከመሪዎች ጋር እያደረጉት ያለው የሁለትዮሽ ውይይት በዲፕሎማሲው መስክ ለኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ገለጹ።
የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች የሚያስገኝ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የአፍሪካ-አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ዲሲ ይገኛሉ።
ከጉባዔው በተጓዳኝ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ- አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና መሪዎች ጋር የሚያደርጉት ውይይት በዲፕሎማሲ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በተለይም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ፤ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማካሄዳቸው በተለይም በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነቱን ይበልጥ የሚያጠናክር ስለመሆኑ ጠቅሰው ሀገራቱ በብዙ መልኩ ተቀራርበው ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምርቶች በአሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ገበያ /አጎዋ/ ዳግም መቅረብ እንዲችሉ ለሚደረገው ጥረትም አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በርካታ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን በማመቻቸት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሪዎች ደረጃ የተደረገው ግንኙነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርም አጋዥ እንደሚሆን ጠቅሰዋል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በመሪዎች የውይይት መድረክ አጋጣሚውን በመጠቀም ከተለያዩ አገሮች ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አምባሳደር ጥሩነህ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገናል ሲሉ አስታውቀዋል።