ቀጥታ፡

የግመል ወተት ምርታማነት ለማሳደግ ለተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ልማት ትኩረት ተሰጥቷል-ቢሮው

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ህዳር 5/2015  በሶማሌ ክልል ከግመል የሚገኘውን የወተት መጠን ለማሳደግ ለተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ልማት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ግብይት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አህመድ አዋሌ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከአንድ ግመል በቀን የሚመረተው የወተት መጠን ከሁለት እስከ አራት ሊትር ብቻ ነው።

የግመል ወተት ምርታማነት ለማሳደግ በመኖ አቅርቦት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት የወንዞች ተፋሰስ አከባቢ የሚገኙ 16 ሺህ ከፊል አርብቶ አደሮችን በማሳተፍ  በ24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።

አሁን ላይ  ለተሳታፊ ከፊል አርብቶ አደሮች የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎች ለማቅረብና  የሙያ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።

የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በክልሉ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ እንደሚደረግ አቶ አህመድ አስታውቀዋል።

ጅግጅጋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ፈረህ የግመል ወተት እርባታ  ማህበር ስራ ኢስኪያጅ ወይዘሮ ፈረህ አብዲወሊ 550 የወተት ግመሎችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብና የተመጣጠነ መኖ እንዲመገቡ በማድረግ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

አሁን ላይ  ከአንድ ግመል በቀን እስከ ስድስት ሊትር ወተት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሚያረቧቸው ግመሎች መካከል 120 ያክሉ የሚሰጡትን ወተት ለጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም ወደ ጎረቤት ሀገር ለመላክ እቅድ እንዳላቸው አመላክተዋል ።

ለፉት አራት ወራት በሶማሌ ክልል በኩል ለውጭ ገበያ ከቀረበ 57 ሺህ 160 ሊትር የግመል ወተት ከ46 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም