የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ። ሁለቱ ሚኒስትሮች በኒውዮርክ ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውንና በሚያጠናከሩባቸውና በቀጣናው ባሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ወሳኝና ዘርፈ-ብዙ ለውጦችን እያካሄደ ነው ሲሉ ዶክተር ወርቅነህ በወቅቱ ገልጸዋል፡፡ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማትን መገንባትም የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸው አሜሪካ ይህን ሂደት እንድታግዝ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡ የአሜሪካ ባለሀብቶችንም በኢትዮጵያ ያሉትን ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲጠቀሙባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ አድንቀው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በትብብር ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡