በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትሕን በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል- የህግ ባለሙያ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትሕን በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል- የህግ ባለሙያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 04/2015 የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ፍትህን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ስለሚኖረው ለተግባራዊነቱ ሁሉም ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሃት የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።
የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዴዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የስምምነቱን አተገባበር በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ ተዓማኒና ግልጽ የሽግግር ፍትሕ እንደሚፈጸም ገልጸው ከተያዘው ወር ጀምሮ ሁሉንም አካላት ያካተተ ሰፊ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃሳባቸው በሚሰማበት እና የበኩላቸውን ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታን በሚያረጋግጥ መልኩ ተዓማኒነት ያለውና ሁሉን አቀፍ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ቀድሞ ለተፈፀሙ ሰፋ ያሉ የመብት ጥሰቶችና ጥፋቶች ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን ዓላማውም የተበዳዮችን በደል ዕውቅና መስጠት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው ሠላም፣ እርቅና እውነተኛ ዴሞክራሲን ማስፈን ነው።
የህግ ባለሙያና አማካሪ አቶ ተዋነይ ሙላቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሽግግር ፍትህን በርካታ አገራት ተጠቅመውበት ውጤት አግኝተውበታል።
የሽግግር ፍትህ ሰላምና ፍትህን አስተሳስሮ የመሄድ ጉዳይ ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የማይተካ ሚና እንዳለውና በሂደቱም የይቅርታና ምህረት ጉዳዮች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
በጦርነት የተጎዱ አካላትን የማቋቋም እና ካሳ በሽግግር ፍትህ እንደሚታዩ ጠቁመው፤ በዚህም ዘላቂ ማህበራዊና ኢኖሚያዊ መረጋጋት እንደሚመጣ አንስተዋል።
የተለያዩ አገራት ከነበሩባቸው በርካታ ቀውሶች ወጥተው ወደ ሰላም የመጡበት ሂደት መሆኑንም በማውሳት የዘርፉ ባለሙያዎችን ባካተተ መልኩ በቁርጠኝነት ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።