በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ታህሳስ 04/2015(ኢዜአ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ ሊያሳይ እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በቀጣዩ ቀናት ከምስራቅ አውሮፓ የሚገባው ደረቅና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ ሁኔታን የሚጨምር ይሆናል።
በዚህም ሳቢያ በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ደረቃማው የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥልና በተለይ በደጋማ የአገሪቱ ክፍሎች የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ ሊያሳይ እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ሆሮ ጉድሩ፣ እና ምስራቅ ወለጋ፣ ከደቡብ ክልል ቤንች ማጂ እና ባስኬቶ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከጋምቤላ ክልል የመጀንግ እና አኙዋክ ዞን ምስራቃዊ አካባቢዎች ላይ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።
በተጨማሪም የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ላይ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት የደመና ሽፋን የሚኖራቸው ሲሆን በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ መጠነኛ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ።
የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ ሆነው እንደሚቆዩ ይጠበቃል።
በዚህም በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው ደረቃማ የአየር ሁኔታ በመከናወን ላይ ለሚገኘው የሰብል ስብሰባና ድህረ-ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ በጎ ጎን እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
ከደረቃማውና ነፋሻማ አየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ደጋማ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ቅዝቃዜው በቀጣይነት እንደሚስተዋል የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይህም ሙሉ ለሙሉ እድገታቸውን ላልጨረሱ ሰብሎች እንዲሁም በመስኖ በመታገዝ በሚለሙ የፍራፍሬ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች ላይ አሉታዊ ጎን ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል።
በሌላ በኩል በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት የመፈጠር ዕድል ሊኖረው እንደሚችልና በተጨማሪም በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ላይ አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ መጠነኛ እርጥበት ያገኛሉ ተብሏል።
ይህም ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር ጠቃሜታ ይኖረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የላይኛውና መካከለኛው ባሮአኮቦ፣የመካከለኛው እና የታችኛው ኦሞጊቤ፣ የስምጥ ሸለቆ እንዲሁም በጥቂት የመካከለኛው አባይ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የተቀሩት የአገሪቱ ተፋሰሶች በአብዛኛው ደረቅና ከፊል ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ ይጠበቃል።