ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 4/2015 ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተደረገ ባለው ትግል ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያሳሰበ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመከላከል ተራማጅ እና ተግባር ተኮር የመፍትሔ እርምጃዎችን ወስዳለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ላበረከቱት የአመራር ልህቀት አሜሪካን አካዳሚ ኦፍ አቺቭመንት እና ግሎባል ሆፕ ኮአሊሽን የተሰኙ ተቋማት በዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጁት መርሐ-ግብር ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ የላቀ አመራር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጹሁፍ ተቋማቱ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እንደ አፍሪካ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ እውቅና ሰጥተዋል ብለዋል።
ለአረንጓዴ አሻራ ስራዎች የሚሆን ፈንድ እየተዘጋጀ መሆኑንና የካርቦን ንግድ እቅዶችን በመንደፍ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሩ ተጨማሪ ፋይናንስ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመርሐግብሩ በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትን በማፋጠን ዓለም አቀፍ እድገትና ስነ ምህዳር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አፍሪካ በበርካታ ስኬታማ ታሪኮች ተሞልታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካውያውን ሁልግዜም የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚሹ ችግሮች ባለቤት ናቸው የሚለው አመለካከት ጊዜው ያለፈበት እሳቤ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎችን መከላከሉን ቀጥሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተራማጅ እና ተግባር ተኮር የመፍትሄ እርምጃዎችን ወስዳለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ስታስጀምር መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ለንቅናቄው መነሳታቸውን አስታውሰዋል።
በአራት ዓመታት ውስጥ 25 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ የ25 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸው ይህም በነፍስ ወከፍ አንድ ግለሰብ በአራት ዓመታት ውስጥ 250 ችግኞችን መትከሉን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራው የተከናወነው ኢትዮጵያን በደን የማልበስ ስራ የበካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁ 64 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን ለአንድ ዓመት ከመንገድ ዞር እንደማድረግ ይቆጠራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከአማዞን ቀጥሎ ትልቁ የደን መልሶ ማልማትና የደን ሽፋን ፕሮግራም ነው ብለዋል።
ከአዳዲስ ከችግኝ ተከላው እና ከደን ልማቱ ጎን ለጎን በ700 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኙ የብዝሃ-ሕይወት እና በካርቦን የበለጸጉ የተፈጥሮ ደኖችን ወደ ዘላቂ እና አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት ማካተት መቻሉንም ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ብር ቀድሞ ከነበረበት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች በሶስት እጥፍ ከፍ በማድረግ ከ121 ሺህ በላይ ችግኞችን በማፍላት ከ750 ሺህ በላይ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በተለይ ሴቶች እና ወጣቶች ከስራ እድል ፈጠራው ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር በመትረፍ የድንበር ተሻጋሪ የስነ-ምህዳር አስተዳደርን ለማጠናከር አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር ችሏል ብለዋል።
የችግኝ ተከላው በመቶ ሺዎች ቶን የሚቆጠር የካርቦን ልቀትን እንዲሁም የደን መራቆትን ለማስወገድ ሚና የሚኖረው ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚደረገው ትግል ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ አስተዋጽኦ በየትኛውም የአለም አቀፍ መስፈርት የሚደነቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በራስ ጥረት እና የፋይናንስ አቅም መደረጉ ሊደነቅ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የአፍሪካ የላቀ አመራር” ሽልማት ላበረከቱላቸው ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።