የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ 11ኛ ስብሰባውን በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ 11ኛ ስብሰባውን በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀመረ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 4/2015 የምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ስትሪንግ ኮሚቴ 11ኛ ስብሰባውን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀመረ።
በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስተባባሪነት በተጀመረው የኮሚቴው ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፕሮጀክቱን እየተገበሩ ያሉ አምስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ኮሚቴው ከዛሬ ጀምሮ በሚኖረው የአራት ቀናት ቆይታ የስደተኞች ተጽኖ ምላሽ ፕሮጀክት በነበረው የመጀመሪያ ዙር የአምስት ዓመት ቆይታ የተከናወኑ የልማት ዕቅዶች አፈጻፀምና ውጤትን ይገመግማል ተብሏል።
በተጨማሪም በአፈጻጸም ዙሪያ የተገኙ መልካም ተሞክሮችና ልምዶችን በቀጣይ በሁለተኛው ዙር በሚሰፉበት ሁኔታ ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ የትኩረት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በስብሰባው ላይ የኢጋድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የሱማሊያ፣ የጂቡቲና የኡጋንዳ የፕሮጀክቱ አስተግባሪ (ስትሪንግ) ኮሚቴ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናችው።