የቀጣናው ድንበር ዘለል ወንጀሎች - ኢዜአ አማርኛ
የቀጣናው ድንበር ዘለል ወንጀሎች
በአየለ ያረጋል
- የመንግሥታቱ ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር ዘለል ወንጀሎችን ፍሰት በአራት አቅጣጫ ፈርጆታል።
- የቀጣናው አገራት በትብብር በአንድ ማዕቀፍ ካልሰሩ፤ የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል፤ ድንበር ተሻጋሪ ችግር እየወለደ ይቀጥላል።
- ኢትዮጵያ በጸረ-ሽብርተኝነት ያላትን የካበተ ልምድ እና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ አግባብ ግጭቶችን የፈታችበትን ልምዷን አካፍላለች።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን የተቸረ፣ በጂኦ-ስትራቴጂክ አቀማመጡ የታደለ ነው። ቅሉ ከግጭትና ጦርነት ቀውስ አዙሪት ያልወጣ፣ ከረሃብ ጠኔ ያልተፋታ አካባቢ ነው። ቀጣናው የድንበር ዘለል ወንጀሎች መናኸሪያ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል መልኩን እየለዋወጠ፣ አድማሱን እያሰፋ... ለዓለም ሕዝብ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ያትታል። ድርጅቱ አደንዛዥ ዕፅ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የእንስሳት አካል ክፍል ዝውውር፣ ባሕላዊ ቅርሶች እና አዕምሯዊ ንብረት ዘረፋ፣ ገንዘብ ማሸሽ፣ የሐሰተኛ ሰነድ ወንጀሎች፣ ሽብርተኝነት፣ ጦር መሳሪያ ዝውውር፣ አውሮፕላን ጠለፋ፣ የባህር ላይ ውንብድናን ... ከድንበር ዘለል ወንጀሎች መካከል ይመድባቸዋል።
ድንበር ዘለል ወንጀል መልከ-ብዙ ነው። የመንግሥታት አቅመ-ቢስነትና የፖለቲካ ልሂቃን የወንጀሉ ተባባሪነት ተዳምሮ አህጉራዊ ሳንካው ሰፊና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል። የመንግሥታቱ ድርጅት እ.አ.አ በ2013 ባወጣው መረጃ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር ዘለል ወንጀሎችን ፍሰት በአራት አቅጣጫ ፈርጆታል። እነሱም፡-
- ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወደ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ የሚደረግ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፤
- ከደቡብ ምዕራብ እስያ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የሚደረግ ሄሮይን አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፤
- ከምስራቅ አፍሪካ ወደ እስያ የሚደረግ የዝሆን ጥርስ ዝውውር፤ እንዲሁም
- አልፎ አልፎ የሚስተዋል የባህር ላይ ውንብድናዎች የሚሉ ናቸው።
በምስራቅ አፍሪካ ሥር ሰደድ ድህነት አለ። ድህነት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መኖሩ ዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ገንዘባቸውንና መረባቸውን ተጠቅመው በቀላሉ ቀጣናውን እንዲያምሱ ዕድል ይፈጥራል።
መንግሥታቱም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል የአቅም ውስንነት አለባቸው። ድህነት እና ደካማ አስተዳደር መኖሩ ደግሞ ሙስና እንዲስፋፋ፣ በቀጣናው የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ወዲያ እና ወዲህ በቀላሉ እንዲንሰራፋ አድርጓል።
ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ሌሎች ክፍላተ-ዓለም የሚደረግ የሰዎች ዝውውር የተበራከተ ቢሆንም አደገኛው እና መጠነ-ሰፊው ግን የአረብ ባህረ ሰላጤን በማቋረጥ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ አረቡ ዓለም የሚደረግ ሕገ-ወጥ ጉዞ ነው።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲበራከት ማለትም አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊና አካላዊ ጥቃትና ዘረፋ እንዲስፋፋ አድርጓል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ለጉልበት ሥራ ክህሎት ሳይኖራቸው፣ ቀይ ባህርን የሚያቋርጡ፣ የየመንን አለመረጋጋት ሳይፈሩ፣ የጉዞውን ፈተና ... እያወቁ ለሥራ ፍለጋ በአዘዋዋሪዎች እጅ ይንከራተታሉ።
ይህን ለቀጣናው 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' የሆነ ችግር የቀጣናው አገራት በትብብር በአንድ ማዕቀፍ ካልሰሩ፣ የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ድንበር ተሻጋሪ ችግር እየወለደ ይቀጥላል። ድንበር ዘለል ቀውስ እየሰፋ ይሄዳል።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት ትብብር ለወንጀል መከላከል
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል 14ቱን የቀጣናውን አገራት ያቀፈ አደረጃጀት ተመስርቷል። ከ24 ዓመታት በፊት የተመሰረተው ተቋምም የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ይሰኛል።
ተቀማጭነቱን በናይሮቢ/ኬንያ ያደረገው ሕብረቱ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር፣ የመረጃ ልውውጥ ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቴጂ ለመንደፍ እና በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በተለይም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት ግብ ይዞ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1998 በኡጋንዳ ካምፓላ ነበር የተቋቋመው።
አባላቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሞሮስና ቡሩንዲ ናቸው።
ሕብረቱ ከኅዳር 25 እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም 24ኛውን ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በአዲስ አበባ አድርጓል። ስብሰባው የአገራቱ ብሄራዊ ፖሊስ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕብረቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የቀጣናው የኢንተርፖል ኃላፊዎች፣ አታሼዎች... "ሽብርተኝነት እና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን የመከላከል ምርጥ የፖሊሲ ተሞክሮዎችን ማስፋት" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
ስብሰባው ሽብርተኝነት እና ሌሎች የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ላይ ያተኮረ ነበር። በተለይም በፖሊስ ተቋማት አቅም ግንባታ፣ በኦፕሬሽንና ሥልጠናዎች ረገድ የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ምክረ-ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። በተለይም በሽብር ወንጀል፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እንዲሁም የእንስሳት ዘረፋን በመከላከል የተከናወኑ ሥራዎች አፈጻጸም ተገምግመዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢንተርፖል ናይሮቢ ቢሮ ኃላፊ እና የሕብረቱ ጽህፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ጌዴዎን ኪሚሉ፤ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ለቀጣናው ስጋት በመሆናቸው ችግሩን ከተናጠል ይልቅ በጋራ መመከት እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ለሰዎች በነፃነት መዘዋወርና ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ ቀጣናውን ወደ መረጋጋት ለመመለስ የአገራቱ የፖሊስ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበው ነበር።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን ጨምሮ የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የቀጣናው ፈተና ሆነዋል ነው ያሉት። እነዚህ ወንጀሎች ለቀጣናው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች መበራከት ምክንያት መሆናቸውን ቀጥለዋልም ነው ያሉት። የወንጀል ተግባራቱን ለመከላከል የየአገራቱ የፖሊስ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ለመገንባትና ብቁ መኮንኖችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን፣ ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመመከት ለቀጣናው ሰላም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ስብሰባውን ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደች ሲሆን ከዚህ በፊት በአውሮፓ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም አስተናግዳ ነበር። በዘንድሮው መድረክ ኢትዮጵያ በፀረ-ሽብርተኝነት ያላትን የካበተ ልምድ እና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ አግባብ ግጭቶችን የፈታችበትን ልምዷን አካፍላለች።
የኤርትራ ፖሊስ ተቋም ተወካይ እና የፖሊስ አካዳሚ መምህሩ ኮሎኔል ሐዲስ ስዩም፤ በአፍሪካ ቀንድ በሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል ግብዓት የተገኘበት ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን የፖሊስ አዛዦች ሕብረት መሪነትን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተረክባለች። ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ፕሬዝዳንትነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተር ጄነራል ዲዩዶኔ አሙሊ ባሂግዋ ተረክበዋል፡፡ ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረቱን ለሁለት ዓመት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ስትሰራ መቆየቷን አውስተዋል። ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይሎችን በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በተለያዩ ጊዜያት በመላክ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ጭምር የራሷን አስተዋጽኦ ማድረግንም እንዲሁ።
በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከቀጣናው አገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ከቀጣናው ተግዳሮች መካከል አንዱ የሆነውን ድንበር ዘለል ወንጀሎች ለመከላከል፤ በቀጣናው የሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
በ24ኛው ስብሰባ ላይ የሕብረቱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ስለመሆናቸውና የአባል አገራት ትብብር እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በአፍሪካ ሕብረት የኢንተርፖል ተወካይ ፍራንሲስ ዣቪየር ኢንተርፖል በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን እና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የሕብረቱ እና የሌሎች ተቋማት ትብብር
ወንጀል ድንበር የለውምና መከላከሉም ሁሉንም ተቋማት ይመለከታል። በርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተዋንያን አሉ። ወንጀል ድንበር አልባ ነው። ሁሉም የሕብረቱ አባል አገራት በቀጣናው ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ለመፍጠር፣ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ቅንጅታቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል። ሽብርተኝነትንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መመከት የቀጣናው አገራት ቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል።
በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ የፀረ-ሽብር ማዕከል የአፍሪካና የአውሮፓ ማዕከል ኃላፊ ዳንኤል ዳምጃኖቪክ 195 አገራትን በአባልነት ያቀፈው ኢንተርፖል በየአህጉራቱ ከሚገኙ የፀረ-ሽብር የቀጣና ማዕከላት መካከል አንዱ በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በተለይም የሽብርተኝነት ስጋት ባለበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚመለከታቸው የአገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ የፖሊስና ሌሎችም ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ስብሰባም በርካታ ባለድርሻ ተቋማት ጋር ለመምከር ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንተርፖል ላለፉት አምስት ዓመታት ከየአገራቱ የጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ ከፖሊስና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሽብርተኞችን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል። በስብሰባው የቀጣናው አገራት የጸረ-ሽብር ትግል ተሞክሯቸውን ያጋሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ልምድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል መከላከል ላይ ከሚሰሩ አካላት መካከል "ሮክ" የተሰኘው ድርጅት በአውሮፓ ሕብረት የሚደገፍ እና ተቀማጭነቱን በሱዳን ካርቱም ያደረገ የሕግ ማስከበር ትብብር ፕሮጀክት አንዱ ነው። ሰሞነኛውን ስብሰባ የተካፈሉት የሮክ ዳይሬክተር ሐርቪ ጃሜት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ከ11 የቀጣናው አገራት ጋር በትብብር ይሰራል። ከ90 በመቶ ያላነሱት በሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰበሰቡ የኢንተርፖል መረጃዎች በሮክ በኩል እንደሚሰባሰቡ ጠቁመው፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በበረታበት ምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ትብብሩን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤቶቿና የዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት
ኢትዮጵያ በታሪክ ያላትን የአፍሪካ አገራትን የማስተባበር፣ ጫናን የመቋቋም ልምዷን በመጠቀም በወንጀል መከላከልና በፀረ-ሽብርተኝነት ትግል በጋራ ትሰራለች። የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት (EAPCCO) እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በትብብር ለመሥራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። በዚህም ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፖሊስ መኮንኖች የተለያዩ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ዕቅድ እንዳላት በቅርቡ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ፤ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የጥፋት ቡድኖች ኢትዮጵያን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ የጥፋት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ያወሳሉ። ከጥፋት ፈጻሚዎቹ መካከል ሸኔ፣ የጉሙዝ ታጣቂዎች እና በጋምቤላ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ቡድኖችን ጠቅሰዋል። ፌደራል ፖሊስ ከመከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ አደረጃጀትን ዓለም አቀፋዊ የፖሊስ ዶክትሪን መሰረት ባደረገ መልኩ የማዘመን እና የላቀ ሕዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፣ የአቪዬሽን ፖሊስ፣ የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ፣ የምድር ባቡር፣ የአድማ ብተና፣ የድንበርና ፀረ-ኮንትሮባንድ፣ የፖሊስ ኮማንዶ እና ሌሎች አደረጃጀቶችን በመምሪያ ደረጃ በማዋቀር የወንጀል መከላከል አቅሙን እያሳደገ ነው።
ውስጣዊ አቅምን ከማጎልበት ባሻገርም ከጎረቤት አገራት የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀትና የጋራ ዕቅድ በማውጣት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፤ የግብርና ምርቶች እና የማዕድን ውጤቶች፣ አደንዛዥ ዕፅና የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ዝውውር በመከላከል ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም እንዲሁ።
በአዲስ አበባ የተካሄደው 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ጠቅላላ ስብሰባ ታዳሚዎችም ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ዘለል ወንጀሎች መከላከል ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው ነበር። ለአብነትም የደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ልዑክ መሪዎች ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ሳዲክ እስማኤል ሲዲጊ፤ ደቡብ ሱዳን ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ያላት ልምድ ለብዙ አገራት ጥሩ ተሞክሮ የሚሰጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታ ኃይል በማሰማራት የመከላከል ትብብሯን እንደምታጠናክር፣ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋርም በቅንጀት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኤርትራ ፖሊስ ተቋም ተወካይ እና የፖሊስ አካዳሚ መምህሩ ኮሎኔል ሐዲስ ስዩም፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በቀጣይ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ የፀረ-ሽብር ማዕከል የአፍሪካና የአውሮፓ ማዕከል ኃላፊ ዳንኤል ዳምጃኖቪክ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድንበር ዘለል ሽብርተኞችን መከላከል የኢንተርፖል ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል። በሰሞኑ ስብሰባም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ትብብራቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በመንግሥት እና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመቀነስ እና የስደተኞችን ፍሰት ለማስቆም ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቅሰው ነበር።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በመዋጋት የኢትዮጵያን የላቀ ሚና አድንቀው ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ይደግፋል ብለዋል።
በመሆኑም ኢንተርፖል በፀረ-ሽብር ግዳጅ አፈጻጸም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም አገራት የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል፤ አገራቱ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብርም ያጠናክራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የሽብር ተገላጭነት ስጋት ካለባቸው አገሮች መካከል መሆኗን ጠቅሰው፤ የመከላከል ሥራው በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት።
ድንበር ዘለል ወንጀልን በጋራ መመከት የአገራት ትልቅ የቤት ሥራ ነው። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀና መረጃ-መር የፖሊስ አገልግሎት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የመረጃ ትንተና አቅምን የሚያጎለብትና ቴክኖሎጂ-መር የሆኑ በትብብር ወንጀልን የመከላከል ሥራዎችን በዘላቂነት ማላቅ ያሻል።