ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስራ ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ተግባር ተኮር ትምህርት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስራ ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ተግባር ተኮር ትምህርት እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 4/2015 የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባሻገር ተማሪዎች ሲመረቁ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ተግባር ተኮር ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ከሆኑት ዶክተር ተክለአብ ቦሎ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ዶክተር ተክለአብ ቦሎ ስራ የሚፈጥር ትውልድ ለመገንባት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዘርፍ ጥሩ ተሞክሮ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ጸጋዎችን በመጠቀም ለተማሪዎች በተለይ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ተግባር ተኮር ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ችግኞችን በግቢው ውስጥ እንዲያፈሉ፣ እንዲተክሉ እና እንዲንከባከቡ በማድረግ ተማሪዎች ሲመረቁ በዘርፉ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባር ተኮር ትምህርት እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ስለግብርና ምርት ግብዓቶች አመራረት ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ግንዛቤ እያስጨበጠ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
ከግቢ ውጭም በዞኑ የተለያዩ የቡና እና ሌሎች አምራች አካባቢዎችን እንዲጎበኙ እያደረገ ግንዛቤ እንዲይዙ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፈተናዎችን መጋፈጥና ወደ እድል የሚቀይር ትውልድ ለመፍጠር ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ለስራ ፈጠራ ዘርፉ ልዩ ትኩረት የሰጡ በርካታ የዓለም ሀገራት በኢኮኖሚያቸው ላይ ትልቅ እምርታ ማምጣታቸውን በማንሳት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ለሀገሪቱ እድገት በዚሁ ዘረፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆች 2030 በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ለመሆን እየሰራ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም የቦንጋ ዩኒቨርስቲን በጎበኙበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ሂደት ጋር አያይዞ እያከናወናቸው ያሉ የግብርና ሥራዎች ተምሳሌት መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
በምርምር የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ጤፍ፣ ቡና፣ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች፣ የወተት ተዋጽዖዎችን፣ የእንስሳት እና የአሣ እርባታ፣ እንዲሁም ለህክምና የሚውሉ ዕጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑንም አድንቀዋል።