የቄስ በሊና ሳርካ ስርዓተ-ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ ታህሳስ 03/2015 (ኢዜአ) የቄስ በሊና ሠርካ ስርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡

በወዳጅነት አደባባይ ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የአስከሬን ሽኝት ተካሂዷል፡፡

በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይም ቄስ በሊና ሳርካ ላለፉት 60 ዓመታት ወንጌል በመመስከርና ትውልድ በመቅረጽ ማሳለፋቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዩናስ ይገዙ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ቄስ በሊና ሳርካ በወንጌላዊያን ቤተክርሰቲያን ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው'' ብለዋል፡፡

ከልጅነት ዘመናቸው ጀምሮ እምነታቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት ያገለገሉ አባት መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡  

በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ቄስ በሊና የህወይት ዘመናቸውን ትውልዱን በማስተማር አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸማቸውን አውስተዋል፡፡

በተለይ ''ለኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን" በሚለው መጽሃፋቸው ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ መልካምነት ያስተማሩ ትውልዱ ጠንክሮ በመስራት አገሩን እንዲለውጥ የሞራል ስንቅ የሚሆን ሃሳብ ያስቀመጡ አባት ስለመሆናቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ዘመናቸውን ፍቅርን በመዝራት ያሳለፉ ናቸው በማለትም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት፡፡

ትውልዱ ከቄስ በሊና መከባበርን፣ ፍቅርን፣እውነትንና ጽናትን እንዲማርም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  

በህይወት ዘመናቸውም ስንፍናን በማውገዝና ላመኑበት ነገር በቁርጠኝነት በመቆም አርዓያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ  ቄስ በሊና ሳርካ አገራቸውን የሚወዱ ለአገር አንድነትና ሰላም ዘመናቸውን የሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም ከእሳቸው አገር ወዳድነትን፣ ለአገር አንድነትና ሰላም መስራት መማር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ቄስ በሊና ሳርካ ከእናታቸው ከወይዘሮ ጀበኔ ሎኮ እና ከአባታቸው ከአቶ ሳርካ ዳኖ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ1933 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ፤ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡

ቄስ በሊና ሳርካ የሶስት ሴት ልጆችና የሶስት ወንድ ልጆች አባት እንደነበሩም የህይወት ታሪካቸው ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም