አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ክንውን እንዲኖረው የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ክንውን እንዲኖረው የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

ታህሳስ 03/2015(ኢዜአ) አገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ ክንውን እንዲኖረው የሚረዳ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ተሳትፎና በአጀንዳ አሰባሰብ አሰራር ዙሪያ ከኃይማኖት ተቋማት፣ አካል ጉዳተኞች ማህበራት፣ የወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ጽንሰ ሀሳቡ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጹሁፍም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ ኮሚሽኑ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረገውን ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ስራውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ክልሎችም ጋር ውይይት በማድረግ በርካታ ጠቃሚ ግብአቶችን ወስዷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ደረጃ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የሚጠቅም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በምክክር ሂደቱ በአንድ ግዜ በርካታ ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረግ ስለማይችል የሂደቱን ተደራሽነት እውን ማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለሥራው መቀላጠፍ የሚያግዙትን ጽህፈት ቤቶች በዩኒቨርሲቲዎች ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም ጠቅሰው ከሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት ተካሂዶ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የካና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መላከ ምህረት ዘካሪያስ፤ የሰው ልጆች በፍቅርና በአንድነት መኖር እንዳለባቸው የፈጣሪ አስተምህሮ ማዘዙን አመልክተው ለምክክርና አብሮነት ሁላችንም ከልባችን ልንዘጋጅ ይግባል ብለዋል።

የአረጋዊያን ማህበርን ወክለው የተገኙት ጌታቸው ዘውዴ፤ ኮሚሽኑ የሚሰጠንን ኃላፊነት ተቀብለን ለተግባራዊነቱ ለመስራት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።