አየር መንገዱ አዲሱን የ"ኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ለመጀመር የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 3/2015  የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱን የ"ኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ለመጀመር የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የደንበኞቹን ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ዘመናዊና ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ  ግንባታ እንደሚያከናውን ከሦስት ዓመት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ባለ ሥፍራ ላይ እንደሚገነባ የተገለጸው ይህ ፕሮጀክት፤ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነጻ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክ ማዕከል እንደሚኖረውም ነው የተጠቆመው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጀመር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡

አየር መንገዱ አሁን ላይ ግንባታውን ለማስጀመር ፈረንሳይ በሚገኝ አንድ ኩባንያ አማካኝነት ጥናት አካሄዶ ማጠናቀቁንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማስጀመር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የፕሮጀክቱን ዲዛይን ለሚሰሩ ኩባንያዎች ጨረታ እንደሚወጣ ጠቅሰው በተያዘው ዓመት ሁሉንም የዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ለመግባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እንደ አስፈላጊነቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ሊገነባ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

አዲስ የሚገነባው "ኤርፖርት ሲቲ" ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክና ለሞጆ ደረቅ ወደብ ቅርብ በመሆኑ ትልቅ የኢንዱስትሪያል ሎጂስቲክ ማዕከል እንደሚሆንም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም