ታሪክ ሰሪው የሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ማነው?

በሙሴ መለስ

በኳታር አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ለአፍሪካ አዲስ ታሪክ የጻፈችበት ውድድር ሆኗል።

ከትናንት በስቲያ በአል ቱማማ ስታዲየም በየሱፍ ኢኔይሲሪ ግብ ፖርቹጋልን 1 ለ 0 በማሸነፍ በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያ አፍርካዊት ሆና ታሪኳን ጽፋለች።

የአትላንስ አንበሶች እውነትም አንበሶች ያስባለውን አዲስ ታሪክ እንድትጽፍ ያደረገው አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ በዚሁ ስኬቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አድናቆትና ሙገሳ እየጎረፈለት ነው።

በፖርቹጋሉ ጨዋታ ወቅት “እኛ የዓለም ዋንጫው አለት ነን” ሲል ከጨዋታው በኋላ ስለ ቡድኑ ጥንካሬ በልበ ሙሉነት አስተያየቱን መስጠቱ ስራን ስለሚያውቅ እንደሆነም ይገለጻል።

ለመሆኑ ታሪክ ሰሪው ዋሊድ ሬግራጉዊ ማናው?

ዋሊድ ሬግራጉዊ እ.አ.አ መስከረም 23 1975 በፈረንሳይ ፓሪስ በምትገኘው ኮርቤል-ኢሶኔስ በተሰኘች አካባቢ ከሞሮኮ ቤተሰቦቻቸው ተወለደ።

ሬግራጉዊ ያደገው በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ሞንትኮንሴል አካባቢ ሲሆን በቤተሰቡ ካሉ ስድስት ልጆች ሶስተኛ ናቸው።

አባቱ መሐመድ አብዱልሰላም ሬግራጉዊ ሁልጊዜ ክረምት በመጣ ቁጥር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሞሮኮ የጠረፍ ከተማ ፊንዴቅ ይወስዱት ነበር።

“ሁሌ በየዓመቱ ለሁለት ወር ወደ ሞሮኮ እንሄዳለን፤ ግዴታም ነበር በሞሮኮ ብዙ ጓደኞች ሊኖሩኝ የቻለውም ለዛ ነው” ሲል ባለታሪኩ ዋሊድ ሬግራጉዊ ይናገራል።

ሬግራጉዊ ያደገበት ሞንትኮንሴል አካባቢን በመወከል ኢሶኔ ከተማ በሚደረጉ ሳምንታዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ይጫወትም ነበር።

የጣልያኑ ኤሲ ሚላንና  የስፔኑ ባርሴሎና ‘ክላሲክ’ በሚል ሲደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ለአሰልጣኙ የማይረሱ ትዝታዎቹ ነበሩ።

ለኤሲ ሚላን ክለብ እንዲሁም ለኔዘርላንዶቹ ኮከቦች ሩድ ጉሌት፣ፍራንክ ሪያካርድና ማርኮ ቫን ባስተን የተለየ ፍቅር ነበራቸው።

ዋሊድ ሬግራጉዊ እግር ኳስን የጀመረው በፈረንሳይ አማተር ሊግ ለሚጫወተው ኮርቤል-ኢሶኔስ ታዳጊ ቡድን ነበር።

በቡድኑ በተከላካይ መስመር የሚያደርገው እንቅስቃሴ የኮርቤል-ኢሶኔስ ከለብ ዋና አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሺያ እይታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

የሬግራጉዊ የልጅነት ጓደኛ አዝዲን ኡስ “አማተር ክለቡ እሁድ ጨዋታውን ከማድረጉ አንድ ቀን በፊት ቅዳሜ ሞንትኮንሴል ከተማ በሚደረገው ውድድር ላይ እንጫወታለን። ለሶስት ወይም ለአራት ሰአት እንጫወታለን በዛም የእግር ኳስን መሰረታዊ ነገሮችና እሴቶች መማር ችለናል።” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

አንድ ቀን እንደ እድል ሆኖ የኮርቤል-ኢሶኔስ ታዳጊ ቡድን ሶስት ልመለከት ሄድኩኝ፤ የሰውነት ተክለ ቁመናን፣ፍጥነትና ክህሎትን ከጠንካራ ስብዕና ጋር የያዘውን ሬግራጉዊን ተመለከትኩ፤ ወደ ዋና ቡድን ወስጄው ለሁለት ዓመት ከተጫወተ በኋላ በራሱ ፈቃድ ክለቡን ለቀቀ’ ሲሉ በወቅቱ የኮርቤል-ኢሶኔስ ከልብ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ሩዲ ጋርሺያ እ.አ.አ 2005 ለፈረንሳዩ ዕለታዊ ጋዜጣ ሊበራሲዮን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ሬግራጉዊ ከኮርቤል-ኢሶኔስ ለቆ ወደ ሌላኛው የፈረንሳይ አማተር ክለብ አርሲ ደ ፍራንስ አቀና።

በአማተር ክለቡ አጭር ቆይታ ካደረገ በኋላ እ.አ.አ በ1999 በወቅቱ በፈረንሳይ ሁለተኛ ሊግ ለሚጫወተው ቱሉዝ የፈረመ ሲሆን አለን ጂሬስ የክለቡ አሰልጣኝ ነበሩ።

እ.አ.አ ሐምሌ 31 ቀን 1999 ቱሉዝ በኮን 2 ለ 1 በተሸነፈበት ጨዋታ ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል። ለክለቡ የመጀመሪያ ግቡንም በዛው ዓመት ኤፍሲ ገንጎን 2 ለ 0 ሲያሸንፉ ማስቆጠር ቻለ። በውድድር ዓመቱ 21 ጨዋታዎችን  በማድረግ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።

ቱሉዝ በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ እ.አ.አ በ2000/01 የውድድር ዓመት ወደ ፈረንሳይ ሊግ 1 አደገ። ለቱሉዝ በውድድር ዓመቱ 16 ጨዋታዎችን አደርጎ አንድ ግብ አስቆጠረ። በዛው ዓመት የሚጫወትበት ክለብ ወደ ፈረንሳይ ሊግ 2 ወረደ።

ሬግራጉዊም እ.አ.አ በ2001 ሌላኛውን የፈረንሳይ ክለብ አጃክሲዮን በነጻ ዝውውር ተቀላቀለ። ክለቡ በወቅቱ ይጫወት የነበረው ‘ሊግ 2 ቢኬቲ’ በሚባል ዲቪዚዮን ነበር።

አጃክሲዮ እ.አ.አ በ2002 ወደ ፈረንሳይ ሊግ አደገ። ሬግራጉዊም ለክለቡ ዋና ዲቪዚዮን ማደግ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ ነበር።

እ.አ.አ ጥር 1 2003 አጃክሲዮ ከፈረንሳዩ ፓሪሰን ጀርሜን ያለ ምንም ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሬግራጉዊ በእግር ኳስ ቆይታው የመጀመሪያውን ቀይ ካርድ ተመለከተ።

ቱኒዚያ እ.አ.አ 2004 ባዘጋጀችው 24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊድ ሬግራጉዊ ለብሔራዊ ቡድን ተመረጠ።

በአፍሪካ ዋንጫው ባሳየው ብቃት በዛው ዓመት በወቅቱ ለስፔን ላ ሊጋ ወደ ሚጫወተው ሬሲንግ ሳንታንዴር ተዘዋወረ።

እ.አ.አ ጥር 22 ቀን 2005 ክለቡ በላሊጋው ከባርሴሎና ጋር ባደረገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰለፈ።

ሬሲንግ እ.አ.አ የካቲት 6 ቀን 2005 በቪያሪያል 2 ለ 1 ባጋጠመው ሽንፈት የቀይ ካርድ ተመለከተ።

እ.አ.አ በ2005/06 ተደጋጋሚ ጉዳቶች ያጋጠሙት ዋሊድ ሬግራጉዊ በሬሲንግ ሳንታንዴር ክለብ የነበረውን ቦታ እንዲያጣ አደረገው።

እ.አ.አ በ2007 ሬግራጉዊ በድጋሚ ወደ ፈረንሳይ በመመለስ በወቅቱ በፈረንሳይ ሊግ 2 ለሚጫወተው ዲዮን ክለብ ፈረመ።

የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ከእ.አ.አ 2007 እስከ 2009 በፈረንሳይ በነበረው ቆይታ በዲዮን፣ግሮኖብል እና ፍሊዩሪ 91 ክለቦች ተጫውቷል።

ዋሊድ ሬግራጉዊ ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ከግብጽ ጋር እ.አ.አ በ2001 በፖርቹጋሉ አሰልጣኝ ሁምቤርቶ ኩዌሎ አማካኝነት ነው።

እ.አ.አ በ2004 ቱኒዚያ ባዘጋጀችው 24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አገሩ ሞሮኮ በፍጻሜው በአስተናጋጇ አገር 2 ለ 1 ስትሸነፍ ተጫውቷል።

እ.አ.አ በ2006 ግብጽ ባሰናዳችው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለአትላስ አንበሶች ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

ዋሊድ ሬግራጉዊ እ.አ.አ ከ2001 እስከ 2009 ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን 45 ጨዋታ አድርጎ አንድ ግብ አስቆጥሯል።

ፍሊዩሪ 91 የዋሊድ ሬግራጉዊ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ያበቃበት ክለብ ነበር።

ሬግራጉዊ እ.አ.አ መስከረም 14/ 2010 በ36 ዓመቱ እግር ኳስ አቆመ። “ፕሮፌሽናል እግር ኳስ መጫወት ባቆምም ለስፖርቱ ካለኝ ፍቅር ልምምድ እየሰራሁኝ አልፎ አልፎ ለፍሊዩሪ አማተር ክለብ እጫወት ነበር” ሲል ገልጿል።

በእግር ኳስ ሕይወቱ በሰባት ክለቦች ባደረጋቸው 204 ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ዋሊድ ሬግራጉዊ ወደ አሰልጣኝነት ሕይወት የመጣው እ.አ.አ በ2012 ነው። በወቅቱ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ራቺድ ታኡሲ ረዳት ሆኖ ተሾመ።

እ.አ.አ ጥቅምት 22 2013 ሬግራጉዊ ከረዳት አሰልጣኝነቱ ለቀቀ።

እ.አ.አ በ2014 የሞሮኮ ኤፍ.ዩ.ኤስ ራባት አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው ሬግራጉዊ ክለቡን እስከ እ.አ.አ 2020 መርቷል። እ.አ.አ በ2020 ደግሞ በጋራ ስምምነት ከክለቡ ለቀቀ።

እ.አ.አ ጥር 22 /2020 የኳታሩን አል-ዱሄል ክለብ የተረከበ ሲሆን በውድድር ዓመቱ የኳታር ሊግ አሸናፊ አደረገው።

ይሁንና አል-ዱሄል እ.አ.አ ጥቅምት 2 2020 በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ በሳዑዲ አረቢያው አል-ታዉን ክለብ 1 ለ 0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ በመሆኑ ከክለቡ አሰልጣኝነት ተሰናበተ።

እ.አ.አ በ2021 ወደ ሞሮኮው ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ያመራ ሲሆን እ.አ.አ በ2021/22 የውድድር ዓመት ክለቡን የሞሮኮን ሊግ አሸናፊ አደረገ። የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖም ተሾሟል።

እ.አ.አ ሐምሌ 28/2022 ዋይዳድ አትሌቲከን ለሞሮኮ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍጻሜ አደርሶ ተሸንፏል።

ሬግራጉዊ እ.አ.አ በ2022 ክለቡን የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ በማድረግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።

የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ እ.አ.አ በ2022 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የዓመቱ ምርጥ ሶስት አፍሪካዊ አሰልጣኝ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሎ ነበር። በወቅቱ የምርጥ አሰልጣኝ ሽልማቱ ወደ ሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ አምርቷል።

ዋሊድ ሬግራጉዊ እ.አ.አ በ2022/23 የውድድር ዓመት የካፍ የኤ የአሰልጣኝነት ፈቃድ አገኙ።

እ.አ.አ ነሐሴ 2022 ዋይዳድ አትሌቲክን መልቀቃቸው ይፋ ሆነ።

ዋሊድ ሬግራጉዊ እ.አ.አ ነሐሴ 31 2022 የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በይፋ ተሾመ። አሰልጣኝነት ሆኖ የተሾመበት ወቅት በኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከሶስት ወር ያነሰ ጊዜ ሲቀረው ነበር።

በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ስድስት ከካናዳ፣ቤልጂየምና ክሮሺያ ጋር የተደለደለችው ሞሮኮ በሰባት ነጥብ ምድቧን በመሪነት አጠናቃ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

የአትላስ አንበሶች በጥሎ ማለፉ ስፔንን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በመግባት አዲስ ታሪክ ሰሩ።

ዋሊድ ሬግራጉዊ አፍሪካዊ ሆነኖ ሩብ ፍጻሜ የገባ አሰልጣኝ በመሆን ለራሱ አዲስ ታሪክ ጻፈ።

ከትናንት በስቲያ በአል ቱማማ ስታዲየም ሞሮኮ ፖርቹጋልን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ አፍሪካዊት አገር ስትሆን ሬግራጉዊ ሌላኛውን ደማቅ ታሪክ ለራሱ፣ ለሞሮኮና ለአፍሪካ መጻፍ ቻለ።

ሞሮኮ በግማሽ ፍጻሜው ከነገ በስቲያ በአል በይት ስታዲየም ከወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይ ጋር ትጫወታለች። ሬግራጉዊም ሞሮኮን ለፍጻሜ በማሳለፍ ሌላ አዲስ ታሪክ የመስራት አጋጣሚን ለማግኘት ይገጥማል።

ዋሊድ ሬግራጉዊ የጨዋታ ታክቲክ አረዳድና ብስለቱ፣ጨዋታ በማንበብ ክህሎቱ፣የተጫዋቾቹን የግል ብቃት አውጥቶ በመጠቀም፣ ጠንካራ የቡድን መንፈስና አልበገር ባይነት የመፍጠር አቅሙ በእግር ኳስ ተንታኞች የሚወደሱለት ብቃቶቹ ናቸው።

ዋሊድ ሬግራጉዊ በፈረንሳይ ቆይታው በኢኮኖሚክስ እና ማህበራዊ ሳይንንስ ዲፕሎማ አግኝቷል። በአሰልጣኝነት ዓለም አቀፍ የኤ የአሰልጣኝነት ዲፕሎማ ላይሰንስም አለው።

ሬግራጉዊ የግል ሕይወቱ ሚስጥራዊ የሚባል ሲሆን ስለ ትዳር እና ስለ ቤተሰቡ ምንም አይነት ይፋዊ መረጃ አጋርቶ አያውቅም።

“የአፍሪካ አገራት በዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ እና ለግማሽ ፍጻሜ መድረስን እንደ ትልቅ ግብ ሊያዩት አይገባም፤ ይልቁንስ የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ እንችላለን በሚል ስነ ልቦና መዘጋጀት አለባቸው” ሲል ዋሊድ ሬግራጉዊ መግለጹ ይታወቃል።

የ47 ዓመቱ ሬግራጉዊ የዓለም ዋንጫውን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ይዞ ይመጣ ይሆን?

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም