ቀጥታ፡

በብሪታንያ የሚገኙ የቢዝነስ ባለቤቶችና የሥራ ፈጣሪዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3/2015 በብሪታንያ የሚገኙ የቢዝነስ ባለቤቶች፣ የሥራ ፈጣሪዎችና የኢንዱስትሪ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ።

በብሪታንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢንቨስት አፍሪካ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ሴሚናር አካሂዷል።

በሴሚናሩ የተመረጡ የቢዝነስ ባለቤቶች፣ የሥራ ፈጣሪዎች፣ የኢንዱስትሪ ኃላፊዎች፣ የጤና ተቋማት መሪዎችና የዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ኢትዮጵያ ያለችበትን ቀጣና ስትራቴካጂካዊ ጠቀሜታ እንዲሁም የአለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫነቷን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት በብሪታንያ የሚገኙ የቢዝነስ ባለቤቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ስለሚሰማሩበት ሁኔታ በቂ ማብራሪያ ሴለማግኘታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም