በመሬት ዘርፍ የሚስተዋለውን ሌብነት በዘላቂነት ለመቅረፍ በሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመሬት ዘርፍ የሚስተዋለውን ሌብነት በዘላቂነት ለመቅረፍ በሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 3/2015 በመሬት ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን ሌብነት በዘላቂነት ለመቅረፍ በሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ገለጹ።
ሙስና በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ እየተስፋፉ ከመጡ ወንጀሎች መካከል ዋነኛው ሲሆን፤ ዓለማችን በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በሙስና ኪሳራ እንደሚገጥማት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአፍሪካ ህብረት መረጃ መሰረትም አፍሪካ በሙስና ምክንያት በዓመት 148 ቢሊየን ዶላር የምታጣ ሲሆን፤ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ደግሞ የችግሩ ዋነኞቹ ገፈት ቀማሾች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ሙስና እና የተደራጀ ሌብነት ለኢትዮጵያ የደኅንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን መግለጻቸው ይታወሳል።
መንግሥት ሙስናን ለመከላከል ከሚወስዳቸው እርምጃ በተጓዳኝ ችግሩን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ ማድረግ ላይ እንደሚሰራም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ያስታወቁት፡፡
ይህን ተከትሎም ሙስናን ለመከላከል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሙስና እና የተደራጀ ሌብነትን በመከላከል ረገድ መንግሥት አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ኮርፖሬሽኑ የፀረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር የበኩሉን ሚና ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በተለይ መሬት ዋነኛ የሀብት ምንጭ በመሆኑ ዘርፉን በዘላቂነት ከሙስና የፀዳ ለማድረግ የሰው ኃይል ግንባታና የቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሙስና አገርን በኢኮኖሚ ከማድቀቅ ባሻገር በሕዝብና መንግሥት ያለውን መተማመን እንደሚሸረሽር ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የፀረ-ሙስና ትግሉ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
መንግሥት በሙሰኞች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡