ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፖፕሌሽን ፈንድ አስር አምቡላንሶች ለጤና ሚኒስቴር አስረከበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 3/2015 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፖፕሌሽን ፈንድ በድጋፍ የተገኙ አስር አምቡላንሶችን ለጤና ሚኒስቴር አስረከበ።

የአምቡላንሶቹ ድጋፍ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

አምቡላንሶቹ ለአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚሰጡ ይሆናል።ድጋፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፖፕሌሽን ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ሱዛን ማንዶንግ ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ አስረክበዋል።

አምቡላንሶቹ በካናዳ፣ በጃፓንና በአይሪሽ መንግስታት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፖፕሌሽን ፈንድ የተለገሱ ናቸው።

ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለመገንባት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

ሱዛን ማንዶንግ በበኩላቸው አምቡላንሶቹ ዘመናዊ ግብዓት ያሟሉ በመሆናቸው በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ለሚኖሩ እናቶችና ህጻናት ሞት ምጣኔ ቅነሳ ስራዎች ድርሻው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም