በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 400 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 400 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 03/2015 በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስንዴ በማልማት 400 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ የዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ዛሬ በክልል ሎካ አባያ ወረዳ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በዘንድሮ በጋ ባጠቃላይ ከ67 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ይለማል፡፡
ከሚለማው ውስጥ 10 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ ዘር የሚሸፈን መሆኑን ገልጸው 400 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአርሶ አደሮች በተጨማሪ ባለሀብቶች ወደ ልማቱ እንዲገቡ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በባለሀብቶች በሰፋፊ ማሳ ላይ የሚለማው ስንዴ ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከሚያስገኘው ምንዛሬ በተጨማሪ ማሳዎች ላይ ተቀጥረው ለሚሰሩ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በቅድመ ዝግጅት ወቅት በስንዴ ልማቱ ዙሪያ ለግብርና ባለሙያዎች ሥልጠና እንዲሁም ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን አመልክተዋል።
ግብዓት የማቅረብ ሥራም እንደዚሁ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን ለ4 ሺህ ሄክታር ለቆላማ አካባቢ የሚስማማ የስንዴ ዘርን ጨምሮ ማዳበሪያ መቅረቡን አብራርተዋል፡፡
በቢሮው የእርሻ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በተለይ ባለሀብቶች በልማቱ ላይ በስፋት መሰማራታቸው በአካባቢያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮች በቂ ግንዛቤ፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉበት ሰፊ እድል እንደሚፈጠርላቸው አስረድተዋል፡፡
የዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ እንደሆነ ጠቁመው ከዓምናው ትምህርት በመውሰድ ሥራው እንደተጀመረ ገልፀዋል፡፡
አምና በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሲጀመር በ138 ሄክታር መሬት ላይ እንደነበር ጠቅሰው የልምድ ማነስ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የውሀ እጥረት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በሄክታር እስከ 27 ኩንታል ስንዴ መገኘቱን ጠቁመው በቂ ውሃና ቴክኖሎጂ መጠቀም ከተቻለ 40 ኩንታልና ከዚያ በላይ ምርት ማግኘት የሚያስችል ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
"ዘንድሮ በተለይም ቀደም ተብሎ በተሰሩ የጥናት ሥራዎች የውሃ አማራጮችን የመለየትና አቅርቦትን የማሳደግ ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል፡፡
ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን የማስቆፈርና ወንዞችን ለሥራው ምቹ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ጠቅሰው በሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ 400 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተከናውኖ የዝርጋታ ሥራ መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በሎካ ዐባያ ወረዳ አባያ ዙሪያ ቀበሌ በአቶ በላይነህ ክንዴ በ406 ሄክታር መሬት ላይ ዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ መልማት ተጀምሯል፡፡
በድርጅቱ ውስጥ የእርሻ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ደነቀ ባልቻ በአካባቢው ለእርሻ ሥራ ከተረከቡት 550 ሄክታር መሬት ላይ 406 ሄክታሩን ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዝግጁ በማድረግ ዘር መዝራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
"ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂና ሌሎች ድጋፎችን ከማድረግ ባለፈ የመሠረተ ልማት ችግሮቹን ለመፍታት እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡
ድርጅቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የውሃ ጥናት ሥራ ሰርቶ እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው ለመብራት አገልግሎት ዝርጋታ የሚውሉ ምሰሶዎችን ወደ ስፍራው ማጓጓዝ መጀመሩን ጠቅሰዋል ፡፡
አቶ ደነቀ አክለው ድርጅቱ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው የሚፈልገው የሰው ኃይል መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ አመላክተዋል፡፡
ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል ረጋሳ ቡሪሶ "እንደ ሀገር የተጀመረው የስንዴ ልማት እንቅስቃሴ ወደ አካባቢያችን እንዲመጣ በጉጉት ስንጠብቅ ነበር" ብለዋል፡፡
"ባለሀብቱ ወደኛ አካባቢ ከመጡ በኋላ ብዙ ጥቅሞችን እያገኘን ነው" ያሉት አርሶ አደር ረጋሳ "ከዚህ በፊት በበሬ እናርስ የነበርነው አሁን ላይ በትራክተር ማረስ ጀምረናል" ብለዋል፡፡
በአካባቢያቸው ያሉ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ስንዴ ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው "የባለሀብቱን ትራክተር በመጠቀም እስካሁን 101 ሄክታር መሬት በማረስ በዘር ለመሸፈን ማዘጋጀት ችለናል" ብለዋል፡፡