ቀጥታ፡

በጣና ሀይቅ በዘመናዊ ጀልባዎች አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው- ኢባትሎአድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 3/2015 በጣና ሀይቅ ደረጃውን የጠበቀ ወደብ በመገንባት በዘመናዊ ጀልባዎች ፈጣንና ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) ገለጸ፡፡

የዓለም ስልጣኔ በውሃማ አካላት ዳርቻ ላይ በተመሰረተበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና እንኳን እስካሁንም ከዝናብ ተኮር አመራረት አልተላቀቀም፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ሀይቆችና የወንዝ ዳርቻዎች እስካሁን በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ይናገራሉ።

ከሀይቆችና የባህር ዳርቻዎች በብዛት ሰዎች እርቀው በመኖራቸው የውሃማ አካላት በተለይም የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል።፡

በመሆኑም የውሃ ሃብቶችን በተለያዩ የልማትና አገልግሎት መስኮች ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሰረት በሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

የጎርጎራ፣ ኮይሻና ወንጪ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ባሮ፣ ተከዜና የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን ለማልማት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ዘርዝረዋል።

የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመዋሃድ ‘’ኢትዮ ፌሪስ ጣና’’ በሚል ስያሜ ስራውን ጀምሯል።

በጣና ሀይቅ ላይ  ደረጃውን የጠበቀ ወደብ በመገንባት በዘመናዊ ጀልባዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱን በጣና ሀይቅ ላይ በመጀመር በቀጣይነት በህዳሴ ግድብና ሌሎችም ውሃማ አካላት ዳርቻዎች ላይ የመጀመር እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመሩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በውሃማ አካላት ዳርቻዎች የሚገነቡ በመሆናቸው ዘመናዊ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውሃማ አካላትን የተከትሎ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የባህር ትራንስፖርት ለመስጠት እድል ይፈጥራሉ ያሉት አቶ ሮባ፤ በጣና ሀይቅ ላይ ለዚህ የሚመጥን ዘመናዊ ጀልባዎችን እንገዛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

በጣና ሀይቅ ላይ አማራጭ የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር እንዘረጋለን፤ ለዚህም ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም