ቀጥታ፡

ሁመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ከሁለት ዓመት በኋላ ኤሌክትሪክ አግኝቷል

አዲሰ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 2 ቀን 2015 ከሁለት ዓመት በላይ ኤሌክትሪክ ተቋርጦበት የቆየው ሁመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል አግኝቷል፡፡

አካባቢው ከሽሬ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ያገኝ የነበረ በመሆኑ አስቸጋሪ መልክዐምድርና የአየር ሁኔታ ያለው የሁመራ - ሽሬ 230 ኪሎ ሜትር ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር ሲጠገን ቆይቷል።

ይሁንና ጥገናው ተጠናቆ ከሽሬ ማከፋፈያ ጣቢያ ለማገናኘት ሲሞከር ከተከዜ ወደ ሽሬ የሚመጣው መስመር ላይ ችግሮች በማጋጠሙ ኃይል ሽሬ ከተማ ማድረስ አለመቻሉን መገለጹ ይታወሳል።

አስቸጋሪ የነበረው የተከዜ መስመር ጥገና ከተጠናቀቀ በኋላ ሁመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ማድረስ ተችሏል።

በመሆኑም ከሁመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ያገኙ የነበሩ ከተሞች በሙሉ ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ አመራር ቡድን በተከናወነው ሥራ የተገኘው ውጤት እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

በቀጣይም ኃይል ያላገኙ አካባቢዎችን መልሶ ለማገናኘት በትኩረት እንደሚሰራ ማስታውቁን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የተላከልን መግለጫ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም