ኢትዮጵያ የፓን- አፍሪካኒዝም መነሻ፣ የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማሳያ አገር ናት- ፕሮፌሰር ቲንሰን ሙጉችኒ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የፓን- አፍሪካኒዝም መነሻ፣ የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማሳያ አገር ናት- ፕሮፌሰር ቲንሰን ሙጉችኒ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 2/2015 ኢትዮጵያ የፓን- አፍሪካኒዝም መነሻ፣ የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማሳያ አገር ናት ሲሉ በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ጥናት ዲን ፕሮፌሰር ቲንሰን ሙጉችኒ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማዕከል (ዩኒሳ) በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 71 ተማሪዎችን ትናንት በዶክትሬት እና በማስተርስ ዲግሪ አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በተለያዩ ማህበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስኮች የተከታተሉ 57 የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው የድህረ-ምረቃ ጥናት ዲን ፕሮፌሰር ቲንሰን ሙጉችኒ ዩኒሳ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2004 በኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የትምህርት ትብብር ስምምነት ውጤት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሰቲው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2009 በኢትዮጵያ በይፋ ሥራውን በመጀመር በማህበራዊ ሳይንስ፣ በምህንድስና፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብርና፣ ጤና፣ ሥነ-ባህሪይ፣ ሕግ እና ቢዝነስ አስተዳደር ዘርፎች በርካታ የሰው ኃይል አፍርቷል ብለዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ግብዓት የሆነውን የሰው አቅም ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፤ የሁለትዮሽ ትብብር ቀጣይነት ማሳያም እንደሆነ ተናግረዋል።
ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ በርካታ ደቡብ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ማግኘታቸውን ያወሱት ፕሮፌሰሩ፤ ኢትዮጵያ የፓን-አፍሪካዊነት መንፈስ መነሻ መሆኗን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አገር እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በመሆኗ ማዕከሉ በኢትዮጵያ እንዲከፈት እንዳደረገው ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ የትብብር ስምምነቶች መካከል፤ ዩኒሳም በምስራቅ አፍሪካ አገራት በፓን-አፍሪካዊነት መንፈስ በትምህርት መስክ አገራቱን እያስተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉን በኢትዮጵያ መክፈቱ በተለይም ልዩ ትኩረት በሚሹ መስኮች የዶክትሬት ተመራቂዎችን በማፍራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትምህርት ለሁሉም ችግሮች መፍቻ መሳሪያ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ቲንሰን ሙጉችኒ፤ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ አፍሪካ የምትፈልገውን የሰው ኃይል በማፍራት ዘላቂ ልማቷን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች አገር እና የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማሳያ መሆኗን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ከምዕራባዊያን ተዕጽኖ የተላቀቀ አህጉራዊ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ ዩኒሳ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በደቡብ አፍሪካ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና የወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር የሺመብራት መርሻ፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙንት ከፀረ-አፓርታይድ ትግል የጀመረ መሆኑን አውስተዋል።
ዩኒሳ በተለይ በትምህርት መስክ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ ዓይነተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት የሁሉም ችግሮች መፍቻ መሳሪያ በመሆኑ ዩኒሳ በሰው ኃይል ልማት በማፍራት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርጻ እየሰራች መሆኑን አውስተው፤ ዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች ለኢትዮጵያና አፍሪካ ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክቱ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ተመራቂዎቹ አዲስ የፓን አፍሪካዊነት የቤት ሥራ በመውሰድ ለአገራቸውና ለአህጉራቸው ሊሰሩ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከአውሮፓዊያኑ 2013 ጀምሮ ማዕከሉ 968 ምሩቃንን ያፈራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 454ቱ በሦስተኛ ዲግሪ፣ 367ቱ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች ናቸው።