የሰላም ስምምነቱ ትሩፋቶች

በአየው ከበደ /ኢዜአ/

ታላላቅ የዓለማችን ፈላስፎች እና ተመራማሪዎች ሰላምን በተለያየ መልኩ ይገልጹታል። የሰላም ጽንሰ ሃሳብ አባት እየተባለ የሚጠራውና የሥነ­-ማኅበረሰብ ተመራማሪው ጆሃን ጋልቱንግ ሰላምን “ደስታ፣ ስምምነት፣ እኩልነት፣ ነፃነት እና ፍትህ” ሲል ይገለጸዋል። “ሰላም ሲኖር ምንም የማይመስለን፤ ስናጣው ደግሞ አስፈላጊነቱን አብዝተንም የምንሻው” ነገር ነው ይለዋል። ዋጋውም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይንም ሰላም ጦርነትና ግጭት አለመኖር ብቻ ሳይሆን የፍትህ፣ የህግ እና ሥርዓት መኖር ጭምር እንደሆነ ያምናል። የእንግሊዝኛው ዌብስተር መዝገበ ቃላት ደግሞ ሰላምን “የአዕምሮ እና የልብ መረጋጋት፤ የሰውን ልጅ ከሚያስጨንቁ ነገሮች ነፃ መሆን ብሎም በአጠቃላይ የሰው ልጅ ውሳጣዊና ውጫዊ እረፍት ማግኘት ነው” ሲል ገልፆታል፡፡  ኢትዮጵያውያን የሰላም ዋጋን ጠንቅቀው ያውቁታል።

ግጭት በህይወት የመኖር ማሳያ ተፈጥሯዊ የተቃርኖ ዕውነታ ቢሆንም ለሰው ልጆች ሰላም ሲባል በአዎንታ የሚደገፍ አይደለም። ዓለማችን በተለያዩ ዘመናት በርካታ ግጭቶችን አስተናግዳለች እያስተናገደችም ትገኛለች። እንዲያም ሆኖ ከግጭቶች በኋላ የሚገኘው ሰላም ዘለቄታ እንዲኖረው ለማድረግ ሲባል ግጭቶችን በሰላማዊ ንግግር እና ድርድር መፍታት አዋጭ ስለመሆኑም ይነገራል።

በርካታ የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ ግጭቶች እና አለመግባባቶች መቋጫ መንገድ ንግግር እና ድርድር ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ችግርም እልባት ያገኘው በድርድር ሂደት መሆኑ ከግጭት በኋላ የሚገኘው ሰላም ዘለቄታ እንዲኖረው ያደርጋል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመንግስት እና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሩትን ጫናዎች የሚገፍ ስምምነት መሆን ችሏል። ከስምምነቱ ኢትዮጵያ ብዙ አትርፋለች። በስምምነቱ የሠላም ወጋገን መፈንጠቅ ጀምሯል። የሰላም ስምምነቱ ትሩፋት ግን በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በስምምነቱ ማግሥት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ማትረፍ የቻሉባቸው በርካታ መስኮች ተስተውለዋል። ለማሳያ ያህል ጥቂቶቹን መዳሰስ ተገቢ ይሆናል።

ተኩስ ማቆም እና ጥላቻን ማስወገድ

በኢኮኖሚክስ እና ሰላም ኢንስቲትዩት (Institute for Economics and Peace-IEP) የተዘጋጀው የ2022 የዓለም አቀፍ የሰላም መረጃ ጠቋሚ Global Peace Index (GPI) የዓለም አቀፍ ሰላማዊነት መሪ መለኪያ የአገራት ሰላማዊነት ደረጃ ኢትዮጵያ ከ163 ሃገራት 149ነኛ ደረጃ ይዛለች።

የምሥራቅ አፍሪካ የሠላም መልህቅ በሚል ስትገለጽ የነበረችው ኢትዮጵያ ሰላሟ ደፍርሶ መቆየቱ ይታወሳል። አሁን ላይ ሁኔታው ተለውጧል። የሰላም ስምምነትም ተፈርሟል። እናም በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚለውጥ አጋጣሚ ተፈጥሯል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በዋናነት ያስገኘው ፋይዳ ይከሰት የነበረውን ተጨማሪ ጥፋት እንዲገታ አስችሏል። የአገሪቷ የሰላማዊነት ገጽታም እንዲለወጥና እንዲሻሻል የሚያደርግ ጭምር ነው።  ግጭቱ ጎልቶ ይታየባቸው የነበሩ አካባቢዎችም ከጦርነት ቀጣናነት ተላቀው ወደ ሰላም መረጋጋትና ልማት እንዲሁም መልሶ ግንባታና መቋቋም ፊታቸውን መልሰዋል። ህዝቡም የሰላም ተስፋ ሰንቆ በአዲስ መንፈስ ለመልሶ ግንባታ ወገቡን ማጠባበቅ ይዟል። ከሁሉም በላይ ግን በግጭቱ ለተፈናቀሉና ለምግብ አጥረት ለተጋለጡ ዜጎች ያልተቋረጡ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት ማድረስ የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሯል። 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ እንዳስታወቀው የሰላም ስምምነቱ በታቀደለት መንገድ እንዲፈጸም መንግሥት እየሠራ ይገኛል። በዚህም በትግራይ አማራ እና አፋር አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንና ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ መሰረተ-ልማቶችን መጠገንና አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ መሆናኑን ይፋ አድርጓል።

የህወሓት ትጥቅ መፍታት

የፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት በኬንያ መዲና ናይሮቢ ቀደም ሲል በፕሪቶሪያው ለተደረሰው የግጭት ማቆም ስምምነት ማስፈጸሚያ የሚሆን ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል። ሰነዱ ህወሓት ትጥቅ የሚፈታበትን ዝርዝር ሁኔታ ያካተተ ነው። በስምምነቱ መሰረት የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው የነበሩትን አካባቢዎች በመልቀቅ የፌዴራል መንግሥት እንዲቆጣጠራቸው እንዲሁም የህወሓት ኃይሎች ወደ ካምፕ መግባት መጀመራቸው እየተገለጸ ይገኛል። ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ሆነዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን አትራፊ አድርጓቸዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መነቃቃት

ኢትዮጵያ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት በነበሩ ዓመታት በአፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መዳረሻ ከሆኑ አገራት መከካል ተጠቃሽ እንደነበረች አይዘነጋም። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ችግር የኢንቨስትመንት መዳረሻ ግለትን አቀዛቅዞት ስለመቆየቱ የመንግሥታቱ ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባዔ (UNCTAD) ይፋ ያደረገው ሪፖርትም ይጠቁማል። 

የድርጅቱ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አዝማሚያዎች መከታተያ (Global Investment Trends Monitor) ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቅናሽ መመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ለዚህ መቀነስ በምክንያትነት የተጠቀሰው ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው ችግርና ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ተጽዕኖ እንደነበር ያመላክታል። ሌላው ችግር መፈጠሩን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል እንድትሰረዝ መደረጓ የሚጠቀስ ነው።

በተደረሰው የሰላም ሥምምነት አንዱ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰደው በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መነቃቃት መጀመሩ ነው። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን ተከትሎ በርካታ የውጭ ባለ ሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ሙዓለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀ-መንበር የሆኑት ዘመዴነህ ንጋቱም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ። ችግሩን በሰላማዊ ንግግር መቋጨት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት መነቃቃት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ። የሰላም ስምምነቱ በተደረሰ ማግስት የኢትዮጵያ ‘ዩሮ ቦንድ’ ገዢ ኢንቨስተሮች ቁጥር በዓለም ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን በዋቢነት ያቀርባሉ። ዘላቂ ሰላም መስፈኑ አገሪቱ ወደ ቀደመው ፈጣን ዕድገቷ ለመመለስ በጣሙን አስፈላጊ ነው። በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ዓመታትም ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴዋ የመመለስ አቅም እንዳላት የኢኮኖሚ ምሁሩ ዘመዴነህ ንጋቱ ልጸዋል።

ኢትዮጵያ ካለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ቀደም ሲል ለውጭ ባለ ሀብቶች ክፍት ያልነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ጭምር ክፍት እንዲሆኑ ማድረጓ ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። ይህ ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማሳብ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ይሆናል።

የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻሻል እና የጫናዎች መርገብ

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተፈጠርው ችግር ጋር ተያይዞ ከአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ጋር የተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር እና ዓለም አቀፍ ጫና ቀላል አልነበረም። ከኢኮኖሚያዊ ዕቀባ እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የዘለቀ ተጽዕኖ የማሳረፍ ሰፊ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያሳየው ቁርጠኝነት እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጀርባቸውን ሰጥተው የነበሩ ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁኔታውን ዳግም እንዲያጤኑት አስገድዷቸዋል።  

በስምምነቱ ማግስት እንደ አሜሪካ የአውሮፓ ህብረትና አንዳንድ አባል ሀገራት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ሲያደርሱ የቆዩትን ጫና በመቀነስ ሻክረው የነበሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን የማለሳለስ እና ለስምምነቱ ስኬት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል። የሰላም ስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ ቀደም ሲል የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ በድጋፍ እና በብድር ለመስጠት ቃል የገቡትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመልቀቅ ፍላጎት አሳይተዋል። ይህ ሁሉ ትሩፋት እንግዲህ በሰላም መስፈን ምክንያት ዳግም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያገኙት ሆኗል። 

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይብልጥ እንድታጠናክር የሰላም ስምምነቱ በጎ ሚና የነበረው ሲሆን ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከጅቡቲ እና ከሌሎችም ጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን መፈራረም ችላለች፡፡ እንግዲህ ሰላም ሲኖር እንደ አገር እና እንደ ህዝብ የሚገኘው ትሩፋት ቀላል አይሆንም።

ሠላምን ታሳቢ ባደረገ ልማት የህዝቦችን ብልጽግና ማረጋገጥ ያስችላልና ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት ግድ ይላል። ዛሬ የተገኘው ሰላም እና መረጋጋት ዘላቂነቱ የሚረጋገጠው ሁሉም ለሰላም በጋራ ተግቶ ሲሰራና ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅ ሲችል ነው። ሰላም የሚመጣው ከውስጥ ነው፤ ያለዚያ አትፈልጉት የሚለውን ብሂል ኢትዮጵያውያን ሰላማቸው በእጃቸው እንዳለ አውቀው በጋራ ሊሰሩ ይገባል። ከሰላም ትሩፋቱ ለመቋደስ ሰላሙን መጠበቅ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም