የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የሚሰራ የልህቀት ማዕከል ሊያቋቁም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የሚሰራ የልህቀት ማዕከል ሊያቋቁም ነው
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 1/2015 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ በጥናትና ምርምር የሚደግፍ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገለጸ።
ማዕከሉ በዘላቂ ልማት ግቦች አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረገው ፕሮጀክት አካል እንደሆነ አመልክቷል።
ፕሮጀክቱን የኖርዌይ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ የሚደገፍ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦስሎና ማላዊ ዩኒቨርስቲዎች በጋራ የሚተገብሩት እንደሆነ ተገልጿል።
በጥናትና ምርምር፣አጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በመስጠት በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የዘላቂ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍን እንደሚያካትት ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን ከወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱም ፕሮጀክቱ ግቡን እንዲመታ የምክር ቤቱ አባላት ምን ዓይነት ሚና ሊጫወቱ ይገባል? የሚለውን ዓላማን ያነገበ ነው ተብሏል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር አክሊሉ አምሳሉ፤ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ክፍተት ያለባቸውን ቦታዎች በመለየት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የልማት አንቀሳቃሾች በፕሮጀክቱ ተደራሽ የሚደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሳኩ የሚደግፍ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው የልህቀት ማዕከሉ በሦስተኛና ሁለተኛ ዲግሪ ሰልጣኞችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን ነው ዶክተር አክሊሉ ያብራሩት።
የኢትዮጵያን አድገትና ልማት፣የታዳሽ ኃይል ሽግግር እና የምግብ ዋስትናን የተመለከቱ ጥናቶች በማካሄድ ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣መስኖና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አወቀ አምዛዬ፤ ፕሮጀክቱ በተለይም ቅንጅታዊ አሰራሮች እንዲኖሩ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሳዲቅ አደም፤ ፕሮጀክቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ከዋለ ውጤታማ መሆን ይችላል፤ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።