የካፒታል ገበያ ዜጎች አገራቸውንና ራሳቸውን የሚጠቅሙበት አስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓት ነው - የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የካፒታል ገበያ ዜጎች አገራቸውንና ራሳቸውን የሚጠቅሙበት አስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓት ነው - የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 01 ቀን 2015 የካፒታል ገበያ አስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓት በማስፈን ዜጎች አገራቸውንና ራሳቸውን የሚጠቅሙበት የፋይናንስ ስርዓት መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ የሌላት ነገር ግን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ግዙፍ የአገር ውስጥ ምርት ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የካፒታል ገበያ መጀመር የሚያስችል አዋጅ ከአንድ አመት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ መንግስት ስርዓቱን የሚያስተዳድር “የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን’’ የተባለ ተቋም በመቋቋም ላይ መሆኑም እንዲሁ።
ካፒታል ማርኬት በአስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓትና ገበያ መር በመሆኑ የመንግስት የብድር ጫናን ይቀንሳል፣ ባለሀብቶችም መዋለ ነዋያቸውን ያለስጋት እንዲያፈሱ የሚረዳ መሆኑንም ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ደረጄ ደጀኔ፤ ካፒታል ማርኬት ወቅቱ የሚፈልገው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተርና የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ የፋይናንስ ስርዓት መሆኑን ያብራራሉ።
በአስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓትና በገበያ መመራት በተለያዩ የፋይናስ አገልግሎቶች ባለሀብቶች የሚገጥማቸውን ምዝበራ ማስቆም የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የካፒታል ማርኬትን ጠቀሜታ ይበልጥ ለማጠናከር ባለድርሻ አካላት ስርዓቱን በአፋጣኝ መተግበርና ሂደቱ በጥብቅ ዲሲፒሊን እንዲመራ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢንዮስ በርኸተስፋ፤ ካፒታል ማርኬት በአገሪቱ በግልም ሆነ በመንግሥት ለሚካሄዱ ኢንቨስተመንቶች የፋይንስ አቅርቦት በማሳለጥ የዘርፋን እድገት የሚያጎለብት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረችው ላለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት፣ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር ለተያዘው ዕቅድ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።
ካፒታል ገበያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚንቀሳቀስበትና በርካታ ሰዎች የሚሳተፍበት በመሆኑ ዘርፉን የሚመሩ ሰዎች በጥብቅ ዲስፒሊን የሚመሩና በቂ ስልጠና ያገኙ ሊሆኑ ይገባልም ተብሏል።