ቀጥታ፡

ሃሰተኛ የብር ኖቶችንና ዶላር ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 1 ቀን 2015 በጎንደር ከተማ  2 ነጥብ 5 ሚሊዮን  ሀሰተኛ የብር ኖቶችና 95 ሺህ ዶላር ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በከተማዋ ኮሌጅ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-14688(አማ) በሆነ ባለ ሶስት እግር የባጃጅ ተሸከርካሪን በመጠቀም ሀሰተኛ ገንዘቡን በድብቅ ሲያጓጉዙ በህብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማንደር ዋለልኝ አስረድተዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋለው ሀሰተኛ ገንዘብ ውስጥ መጠኑ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሆነ ባለ 200 የኢትዮጵያ ብር ኖቶች እና መጠኑ 95 ሺህ የሆነ ባለ 100 የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።

ሀሰተኛ የብር ኖቶቹ እና ህገ-ወጥ ዶላሩ የተገኘው በተጠርጣሪዎቹ ሻንጣ ውስጥ መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር ዋለልኝ፤ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ የሀሰተኛ ገንዘቡን ምንጭ ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ግብይት ሲፈጽም በሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር እንዳይጭበረበር ጥንቃቄ እንዲያደርግና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥመው ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ኮማንደሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም