ቀጥታ፡

ደኢህዴን ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተፈጸሚነት እንደሚሰሩ እህት ድርጅቶ ገለጹ

ሀዋሳ መስከረም 18/2011 ደኢህዴን በ10ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተፈጸሚነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በማድረግ ለስኬታማነቱ እንደሚሰሩ እህት ድርጅቶ ገለጹ፡፡ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተጀመረው የደኢህዴን 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅቶች ተወካዮች ለደኢህዴን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንዳሉት ደኢህዴን ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለውና አገራዊ ለውጡን በብቃት ለመምራት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ድርጅትና የለውጥ ኃይል ነው። "ብዝሀነት ስጋት ሳይሆን ውበት፤ ችግር ሳይሆን እድልና ጸጋ ነው" ያሉት የኦዴፓ ተወካይ ደኢህዴን በጉባኤው የሚወሰናቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ የደቡብ ክልልን ሰላም ለመንሳት የሚደረገው ማንኛውንም ሙከራ የክልሉን ህዝቦች በማስተባበር መመከት እንደሚቻል ገልጸው ደኢህዴን በጉባኤው ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት ኦዴፓ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አመልክተዋል። የብአዴን ተወካይ አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ደኢህዴን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችንና ልዩልዩ ማንነቶችን አቻችሎ በመምራት ብዝሀነትን እንደትልቅ ጸጋ መጠቀም የቻለና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ተሞክሮ ያለው ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ባዘዘው፣  ደኢህዴን በአዲሱ የለውጥ ጉዞ ለለሚያናውናቸው ተግባራት ብአዴን ከጎኑ በመቆም አጋርነቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ ደኢህዴን ባለፉት 27 ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞው አኩሪ ተግባር መፈጸሙንና በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቡን የገለጹት ደግሞ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ተወካይ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ ናቸው። ደኢህዴን "የህዝቦች አንድነት ለሁለንተናዊ ለውጥ" በሚል መሪ ቃል እያካሄደ ባለው 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው መላውን የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍም አቶ ተወልደ እምነታቸውን ገልጸዋል። ህወሓት ለደርጅቱ ለውሳኔዎቹና ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም