“እኔ እግር ኳስን የምጫወተው ለኔ ሲሉ ሕይወታቸውን በሙሉ ለሰጡኝ እናትና አባቴ ነው። ” ሞሮኳዊው ኮከብ አሽራፍ ሀኪሚ

እድል ጀግኖችን ትጠራለች ለዚህም አሽራፍ ሀኪሚን ጠይቁት ይላል የአልጄሪያው ጋዜጠኛ ማኸር ሜዛሂ ስለ ሞሮኳዊው ተጫዋች ‘Morocco’s Hakimi: From ‘difficult moments’ to World Cup stardom’ በሚል ርዕስ በአልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ።

ሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም የሞሮኮና የስፔን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ እየተካሄደ ነው። ሁለቱ አገራት በ120 ደቂቃዎች ምንም ግብ ባለማስቆጠራቸው ጨዋታው ወደ መለያ ምት አመራ። የጭንቅ ሰአት መጣ።

የፈረንሳዩ ፓሪሰን ጀርሜን የቀኝ መስመር ተጫዋች አሽራፍ ሀኪሚ አገሩ ሞሮኮ በዓለም ዋንጫ አዲስ ታሪክ የምትጽፍበትን የፍጹም ቅጣት ምት ሊመታ ተዘጋጅቷል። የሞሮኮ ደጋፊዎች እና ገልለተኛ ተመልካቾች በደስታና በጭንቀት መሐል ሆነው የፍጹም ቅጣት ምቱን እስኪመታ እየጠበቁት ነው።

አሽራፍ ሀኪሚ የሞሮኮን ትልቅ እና ታሪካዊ አደራ መሸከሙን አልዘነጋውም የመጨነቅ ስሜት ይታይበት ነበር። ስሜቱ ተጫዋቹ ካለበት ኃላፊነት አኳያ ተቀባይነት ያለው ነውና።

ሀኪሚ ወደ ኳሷ አማተረ ፍጹም ቅጣት ምቱን በጫና ውስጥ ቢሆንም ተረጋግቶ በመምታቱ በአስደናቂ ሁኔታ የስፔኑን ግብ ጠባቂ ኡናይ ሲሞንን በማታለል ፓኔካ የምተሰኘውን ቄንጠኛ ግብ በጎሉ መሐል ለመሐል በመምታት አስቆጠረ።

ሀኪሚ ታሪክ ሰራ ሞሮኮን በዓለም ዋንጫ ስድስተኛ ተሳትፎዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሩብ ፍጻሜ አሳለፈ። ታሪካዊ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተከትሎ እርሱና የቡድን አጋሮቹ ደሰታቸውን በፈንጠዝያ ገለጹ። ነገር ግን ሀኪሚ አንድ ነገር አልረሳም። ወደ ደጋፊዎቹ በመሄድም ባለውለታዬ ወደ የሚላት እናቱ ቀርቦ በማቀፍና በመሳም ደስታውን ሲገልጽ ታየ።

አሽራፍ ሀኪሚ በስፔን ላይ ያስቆጠራት ቄንጠኛ ግብ የእግር ኳስ ሕይወቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረበት ነው ብሏል የአልጄሪያው ጋዜጠኛ ማኸር ሜዛሂ በአልጄዚራ ላይ ስለ ተጫዋቹ ባሰፈረው ሀተታ።

እ.አ.አ ሕዳር 8ቀን 1998 በስፔን ማድሪድ ከሞሮኳዊ እናትና አባቱ ተወለደ።
አባቱ ሀሰን ሀኪሚ እና እናቱ ሰይዳ ሙህ ይባላሉ። አሽራፍ ሀኪሚ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የመጣበት መንገድ ረጅም፣ ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑን ጋዜጠኛው ይገልጻል።

ገና ከለጋ እድሜው አንስቶ የኮከብነት ተስፋ የነበረው ሀኪሚ በስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ በስምንት ዓመቱ ተመልምሎ የእግር ኳስ ሕይወቱን አንደ ብሎ ጀመረ።

ሀኪሚ በእግር ኳስ ሕይወቱ ያገኛቸው ስኬቶች “በልፋትና በትጋት ያገኛቸው ናቸው” ሲል አልጄሪያዊው ጋዜጠኛ ስለ ሞሮኮው ታታሪ ተጫዋች ብርታት ይናገራል።

800 ሺህ የሞሮኮ ዳያስፖራዎች በሚኖሩባት ስፔን ያደገው አሽራፍ ሀኪሚ እድገቱ በፈተና የተሞላ ነበር። ሀኪሚ ያደገው በማድሪድ የኢንዱስትሪ ስፍራ እየተባለች በምትጠራው ጌታፌ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦቹ ነው።

በየዕለቱ ወደ ሪያል ማድሪድ ካስቲያ አካዳሚ የሚያደርገው ጉዞ ወደ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ቢያደርሰውም የልጅነት ሕይወቱን “ደስተኛ ነገር በተወሰኑ አስቸጋሪ ፈተናዎች የተሞላ” ሲል ይገልጸዋል። “እናቴ የጽዳት ሰራተኛ አባቴ ደግሞ የመንገድ ላይ ንግድ ይሰሩ ነበር” ሲል ሀኪሚ በስፔን ኤልቺሪንጉዊቶ ከተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር በነረው ቆይታ መግለጹን የአልጄሪያው ጋዜጠኛ ማኸር ይናገራል።

“ሕይወታቸውን ለኔ ሰጥተዋል ከሌሎች የቤተሰቦቼ አባላት ብዙ ነገር በመውሰድ እኔ ስኬታማ እንድሆን ለፍተዋል፤ ዛሬ እግር ኳስን የምጫወተው ለነሱ ነው” ብሏል። አሽራፍ ሀኪሚ በታዳጊነት እድሜው በአውሮፓ የወጣቶች ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ያሳይ የነበረው አስገራሚ ብቃት በሚኖርበት አካባቢ ታዋቂ እንዲሆን አደረገው።

በዛ ታዳጊ እድሜው የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ትኩረት መሳቡን አልጄሪያዊው ጋዜጠኛ ያስታውሳል። በአውሮፓ ያለው የሞሮኮ ዳያስፖራ ትልቅ መሆኑና የሞሮኮ ተጫዋቾች ብቃት በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ፣ ስፔንና ፈረንሳይ አገራት በስፋት መንሰራፋቱን ይገልጻል።

የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይሄንን አጋጣሚ በመጠቀም መልማዮቹን ወደ ስፔን በመላክ ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወት አግባቡት። አሽራፍ ሀኪሚን ለመመልመል ያነሳሳቸው ለሪያል ማድሪድ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ሲያሳይ በነበረው ብቃት እንደሆነ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ናስር ላርጉዌት እ.አ.አ በ2018 ለታዋቂው የእግር ኳስ መጽሔት ፎርፎርቱ በሰጡት አስተያየት አስረድተዋል።

በዚህም አሽራፍ ሀኪሚ እ.አ.አ በ2016 በ18 ዓመቱ ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ። ሀኪሚ ከሞሮኮ የመጀመሪያ ጨዋታው በኋላ ለስፔን ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች የተወሰኑ ጨዋታዎችን ማድረጉ ለስፔን የመጫወት ሀሳብ አለው የሚል ጉዳይ እንዲነሳ አደረገ። ይሁንና ሀኪሚ ለስፔን መጫወት አለብኝ የሚል ስሜት መቼም ተሰምቶኝ አያውቅም ይላል።

“ባህሌ የሞሮኮ ነው፤ ቤት ውስጥ የምናወራው የሞሮኮን ቋንቋ ነው የምንበላው ምግብ የሞሮኮ ነው። እውነት ለመናገር ለስፔን ስለ መጫወት ያን ያህል አስቤ አላውቅም” ሲል ከፈረንሳዩ ለኪፕ መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።

ሀኪሚ ይቀጥላል፤ “የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ እየተመለከትኩኝ ነው ያደጉት፤ አባቴ ስለቀደምት የሞሮኮ ኮከብ ተጫዋቾች ይነግረኝ ነበር” ብሏል።

እ.አ.አ 2017 ሀኪሚ ወደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነት ደረጃ ለመሸጋገር የተዘጋጀበት ወቅት ነው። ያ ጊዜ የሚጫወትበት ክለብ ሪያል ማድሪድ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ያነሳበት ታሪካዊ ወቅት እንደነበር ማኸር ሜዛሂ ያስታውሳል።

በወቅቱ በፈረንሳዊው ኮከብ ዚነዲን ዚዳን በሚመራው ሪያል ማድሪድ ዘጠኝ ጊዜ በላሊጋው የመሰለፍ እድል አግኝቶ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ይሄም ሩሲያ ከአራት ዓመት በፊት ባሰናዳችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ውሰጥ ከመካተት አላገደውም።

የአሽራፍ ሀኪሚ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ አስደሳች አልነበረም። በምድብ ሁለት የነበረችው ሞሮኮ በኢራንና ፖርቹጋል በተመሳሳይ 1 ለ 0 ተሸንፋ ከስፔን ጋር ሁለት ለሁለት አቻ ወጥታ ከምድቧ ተሰናበተች።

የዓለም ዋንጫ ተሳትፎን ያሳካው አሽራፍ ሀኪሚ በእግር ኳስ ሕይወቱ ወደ ትልቅ ደረጃ መሸጋገር እና በሪያል ማድሪድ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባትን ሕልሙ አደረገ። ሀኪሚ እንዳሰበው አልሆነለትም። ሪያል ማድሪድ ለጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ለሁለት ዓመት በውሰት ሰጠው።

የሞሮኮው ኮከብ ዶርትሙንድ በእግር ኳስ ሕይወቱ መነሳሳት ፈጥሮለት በሁለት ዓመት ቆይታው በ73 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ 12 ግቦችን በማግባትና 17 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በማቀበል ውጤታማ የሚባል ጊዜን አሳለፈ።

ይሁንና አሁንም ሪያል ማድሪድ የሀኪሚን ግልጋሎት ለማግኘት ፈቃደኛ አልሆነም።
የስፔኑ ክለብ የተጫዋቹን ለሪያል ማድሪድ የመጫወት ፍላጎት በተደጋጋሚ ውድቅ በማድረጉ ሀኪሚ እ.አ.አ በ2020 የጣልያኑን ከለብ ኢንተር ሚላንን ተቀላቀለ።

ኢንተር ሚላን በአሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ እየተመራ ከ10 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴሪ አ ዋንጫን ሲያነሳ አሽራፍ ሀኪሚ ለቡድኑ ስኬት ቁልፍ ሚና መጫወት ችሏል።

በስተመጨረሻ ይላል የአልጄሪያው ጋዜጠኛ ማኸር ሜዛሂ በስተመጨረሻ አሽራፍ ሀኪሚ ከአስቸጋሪው ረጅም የፈተና ጉዞ በኋላ እ.አ.አ በ2021 ወደ ፈረንሳዩ ፓሪሰን ጀርሜን 83 ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ታላቁን ዝውውር በማድረግ ያለው ብቃት እውቅና ማግኘቱን ይናገራል።

የ24 ዓመቱ አሽራፍ ሀኪሚ ያለ ምንም ጥያቄ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ቢባል ማጋነን አይሆንም ይላል ሜዛሂ። ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በወጥነት አስደናቂ ብቃቱን ማሳየቱን ገልጿል።

ጋዜጠኛ ማኸር ሜዛሂ በአልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈረው ሰፊ የተጫዋቹ ግለ ታሪክ ዳሰሳ ስለ ሀኪሚ ባህሪያትም ያነሳል። እንደ ሀኪም ዚዬች እና ኑሳይር ማዝራዊ ያሉ የሞሮኮ ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞ አሰልጣኝ ቫሂድ ሃሊሆድዚች በሚጋጩበት ወቅት የሀኪሚ ባህሪይ ሁልጊዜም ነገሮችን ከማጣጣል ያለፈ እንደሆነ ይገልጻል።

የቦስኒያ ሄርዞጎቪኒያው አሰልጣኝ ሀኪሚ በቡድኑ ውስጥ አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ በማለም ያግዘኛል በሚል በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እንደ መለኪያ መሳሪያ ይጠቀሙበት እንደነበርም ያወሳል።

ቫሂድ ሃሊሆድዚች “የአሽራፍ ሀኪሚ የሰውነት ጮማ መጠን ሰባት በመቶ ነው፤ በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ የሞሮኮ ተጫዋቾች የጮማ መጠን ከ13 እስከ 16 በመቶ ይደርሳል” በማለት ሞሮካዊው ኮከብ አሽራፍ ሀኪሚ ለእግር ኳስ አጨዋወት መቹ የሆነ ተክለ ሰውነት እንዳለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እ.አ.አ በ2021 በካሜሮን አስተናጋጅነት በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ግቦችን ለማግባት ሲቸገር የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሀኪሚ ሁለት ወሳኝ ግቦችን ለአትላስ አንበሶቹ አስቆጥሯል።

ሀኪሚ ያለውን የእግር ኳስ ወጥ ብቃት አገሩ በፈለገችው ወሳኝ ወቅት ሁሉ የበኩሉን በማበርከት አሳይቷል። ሞሮኳውያንም የኮከባቸውን ስኬት ከእንግዳነት አልፎ እንደ ልማድ እያዩት ስለመምጣታቸው ተገልጿል።

ሞሮኳውያን አሽራፍ ሀኪሚ የጨዋታ ደረጃውን ከፍ በማድረግ ሞሮኮን በዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ እንድታልፍ እንዲረዳት አደራ ጥለውበታል ሲል የአልጄሪያው ጋዜጠኛ ማኸር ሜዛሂ ስለ ብርቱውና ስኬታማው ተጫዋች የጻፈውን ዘለግ ያለ ጽሁፍ ቋጭቷል።

አሽራፍ ሀኪሚ በአሁን ወቅት ከስፔናዊታ ተዋናይት ሂባ ሀቡክ ጋር በትዳር በመጣመር ናቢል እና ኡዊዳድ ሀኪሚ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም