መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የጀመራቸውን ጥረቶች አጋር አካላት ሊደግፉት ይገባል- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

122

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ህዳር 30/2015 መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የጀመራቸውን ጥረቶች አጋር አካላት ሊደግፉት እንደሚገባ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ባለፉት 30 ቀናት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ስራ ማከናወን ተችሏል፡፡ 

በቀጣይም የሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽ የማድረጉ ሰራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

በዚህም በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች 145 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬና አልሚ ምግብ ተደራሽ ሆኗል ብለዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ስኬት ይረዳ ዘንድ ያሉትን ሃብቶች ተደራሽ የሚያደርጉ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት የምድርና የአየር ትራንስፖርትን በመጠቀም ሰብዓዊ አቅርቦቱን በተሳለጠ መንገድ እንዲዳረስ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ዓለምአቀፍ ለጋሾች እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች መንግስት በመልሶ መቋቋምና ሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ሊደግፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም