የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የቢራ ገብስ ዝርያ በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ

42

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ''ራስ'' የሚል ስያሜ የሰጠው አዲስ የቢራ ገብስ ዝርያ በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

አዲሱ የቢራ ገብስ ዝርያ በሽታንና ተባይን ተቋቁሞ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችል የማዕከሉ ሃላፊ አቶ ምንተስኖት ወርቁ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህም አርሶ አደሮች ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የቆዩትን ነባር ዝርያዎች ከመተካት ባለፈ እስከ 40 በመቶ የምርት ጭማሪ የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰባት ዓመታትን በፈጀ ምርምር የተገኘው አዲሱ የቢራ ገብስ ዝርያ በብሔራዊ የዘር አጽዳቂ ኮሚቴ በ2013 ዓ.ም. የእውቅና ሰርተፊኬት እንደተሰጠው አስታውሰዋል፡፡

የቢራ ገብስ ዝርያው በቢራ መጥመቂያ ፋብሪካዎች ቤተ-ሙከራዎች የመጀመሪያውን መመዘኛ መስፈርቶች ያሟላ መሆኑን ማረጋጋጫ ማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡   

ምርምር ማዕከሉ የቢራ ገብስ ዝርያውን በዳባትና ደባርቅ ወረዳዎች ባቋቋማቸው የምርምር ጣቢያዎች ማላመዱንና ለአርሶ አደሩ ለማዳረስም ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

ሃላፊው እንዳሉት በ2015/2016 የምርት ዘመን በተመረጡ አርሶ አደሮች የዘር ብዜት ስራ በማከናወን የቢራ ገብስ አልሚ አርሶ አደሮች የገጠማቸውን የምርታማነት ችግር ለመፍታት ያግዛል።

''አርሶ አደሩ ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምባቸው የቆዩ አምስት ነባር የቢራ ገብስ ዝርያዎች አሁን ላይ ምርታማነታቸው እየቀነሰ መጥቷል'' ያሉት ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ተስፋዬ ናቸው፡፡

ነባሮቹ የቢራ ገብስ ዝርያዎቹ በሄክታር 30 ኩንታል ይሰጡ የነበረው በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 10 ኩንታል ዝቅ ማለታቸውን አስረድተዋል፡፡

በዝርያዎቹ ምርታማነት መቀነስ ሳቢያም በዞኑ በ2013/2014 የምርት ዘመን በቢራ ገብስ ሲለማ የነበረው 900 ሄክታር መሬት በ2014/15 ምርት ዘመን ወደ 300 ሄክታር ዝቅ ማለቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታትም የምርምር ማዕከሉ እያመጣው ያለው አዲሱ የቢራ ገብስ ዝርያ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣይ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ማዕከሉ አዳዲስ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ሚናውን እንደሚወጣም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም