ቀጥታ፡

ሩሲያ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ታደርጋለች - ኤቭጌኒ ፔትሮቭን

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  ህዳር 30/2015 ሩሲያ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የሩሲያ የፌዴሬሽን ልዑክ መሪ ኤቭጌኒ ፔትሮቭን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የተካሄደው 8ኛው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የምክክር መድረክ በትላንትናው ዕለት መጠናቀቁ ይታወሳል።

የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የሩሲያ የፌዴሬሽን ልዑክ መሪ ኤቭጌኒ ፔትሮቭን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ሩሲያና ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው።   

በፍጥነት በሚቀያየረው የዓለም ገበያ ውስጥ ሁለቱ ሀገራት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሰፋፊ እድሎች ስለመኖራቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም፣ በሀገራቱ መካከል  በኢኮኖሚው መስክ የተጀመረውን ትብብር ወደ ላቀ የፖለቲካ ግንኙነት በማሸጋገር አዲስ ምዕራፍ ማስጀመር ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለዚህም ሩሲያ፣ያሏትን ሁሉን አቀፍ ልምዶች ለኢትዮጵያ በማጋራት የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

የዓለም የታዳሽ ኃይል ፍላጎት በእጅጉ እንደሚጨመር በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለሩሲያ እያሳየች ያለው አጋርነት በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን በማንሳት፣ ሩሲያ በበኩሏ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የእድገት ፕሮጀክቶች ውስጥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።  

የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የምክክር መድረክ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በማዕድን ዘርፍ እንዲሁም በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሲመክር መቆየቱን ገልጸዋል።

ሩሲያ ያላትን ልምድ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ124 ዓመታት በላይ በጠንካራ ወዳጅነት የዘለቀ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም