በጌዴኦ ዞን በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ32 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል

203

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 በጌዴኦ ዞን በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ32 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዞኑ የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት ከ135 ሺህ ቶን በላይ እሸትና ደረቅ ቡና ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በዞኑ 150 ሺህ አርሶ አደሮች ከ74 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የገለጹት ሃላፊው፤ ለዚህም የተሻለ የቡና አሰባሰብ ስራዎችን በማከናወን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይ የምርት ብክነትን መቀነስና የግብይት ስርዓቱን ማዘመን የተቀመጠውን ግብ ከሚያሳኩ አቅጣጫዎች ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ እንዲያግዝም በዞኑ 202 የሚሆኑ የእሸት ቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ቡና እያዘጋጁ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ከሚሰበሰበው ውስጥ ደግሞ 32 ሺህ ቶን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ዶክተር ዝናቡ አመላክተዋል።

በዞኑ 689 አርሶ አደሮች በቀጥታ የቡና ምርታቸውን መላክ እንዲችሉ ፈቃድ መውሰዳቸውን አክለው ገልጸዋል።

ይህም ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ከማሳደግ ባለፈ አርሶ አደሮችን ለተሻለ ምርታማነት እያነሳሳቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የቡና አልሚ አርሶ አደሮች የገበያ ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱም አንድ አርሶ አደር በነፍስ ወክፍ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ከቡና ሽያጭ ገቢ እያገኙ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ መምሪያው ሃላፊ ገለጻ ባለፈው ዓመት 110 ሺህ ቶን የእሸትና ደረቅ ቡና መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን 25 ሺህ 149 ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘው የቡና ምርት መጠን ደግሞ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ7 ሺህ ቶን በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም