ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና የዳኝነት አካሉ ለሰብዓዊ መብት መከበር በቅንጅት መሥራት አለባቸው-የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

279

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና የዳኝነት አካሉ ለሰብአዊ መብት መከበር በቅንጅት መሥራት ያለባቸው መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ቀን "ሁሉም የሰው ልጆች በነጻነት፣ በእኩልነትና በክብር የመኖር መብት አለው" በሚል መሪ ሃሳብ  የፍትህ ተቋማት በጋራ አክብረዋል።   

ፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ የፍትሕ ተቋማት ተወካዮች በሁነቱ ላይ ተሳትፈዋል።       

ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች አተገባበር ምን ደረጃ ላይ ነው? ምን ክፍተቶች አሉ? እንዲሁም የመፍትሔ እርምጃዎች በመድረኩ ውይይት ተደርጎባቸዋል።  

በሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ግንዛቤ መፍጠርና በትኩረት እንዲሰራበት የማድረግ ጉዳይም በሰፊው ተነስቷል።      

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ፤ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ቢሆንም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሉ በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ነዋይ፤ የሰብአዊ መብቶች በተሻለ መልኩ እንዲተገበሩ ዳኞች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና አተረጓጎም ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።  

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ተወካይ ቻርልስ ኪሞይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በፍትሕ ዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰብአዊ መብቶች መከበር የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ነፃነትና የሰዎችን ክብር በፍትሕ ሥርዓቱ ማስከበር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።           

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰዎችን ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ለሚደረጉ ጥረቶች የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።               

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ቀን በተባበሩት መንግሥታት ጸድቆ መከበር ከጀመረ 75 ዓመታት አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም