ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ የትብብር ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለጸ

19

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ የትብብር ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሞሀመድ ላሜኔ ላባስ የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ደመቀ አጥናፉ አስረክበዋል።

በዚሁ ወቅት ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች ባደረጉት ውይይት በሀገራቱ መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ደመቀ አጥናፉ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ዘርፎች ያላቸውን አጋርነትን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ሃላፊው በመንግስትና በሕወሃትና መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ለአምባሳደሩ ያብራሩ ሲሆን በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች እየተደረጉ ስለሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ መልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ አብራርተውላቸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የድርድር ሂደቶች የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚችሉ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለማበጀት ያላትን ጽኑ አቋም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሞሀመድ ላሜኔ ላባስ በበኩላቸው በመንግስትና በሕወሃት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አድንቀዋል።

አምባሳደሩ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ገልጸው በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም ይህንን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር በአልጄሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወሰ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ደግሞ የአልጄሪያን የ60ኛ ዓመት የነጻነት ቀን ላይ ለመታደም በሀምሌ ወር አልጄሪያ መገኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም