ከሃይቆች በተጨማሪ በሰው ሰራሽ የውሃ ኩሬ የዓሳ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው-የምርምር ማዕከሉ

26

ሕዳር 29/2015(ኢዜአ) ከሃይቆች በተጨማሪ በሰው ሰራሽ የውሃ ኩሬ አማካኝነት የዓሳ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሳ እና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ገለጸ።

የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ እና ተመራማሪ አለማየሁ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የዓሳ ሃብት ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

በዚህም በሃይቆች የዓሳ ማስገር ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስም ህብረተሰቡ በሰው ሰራሽ ኩሬ አሳ በማርባት መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አንድ ዓሳ በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 1 ሺህ 500 እንቁላሎችን እንደምትጥል ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ በአየር ንብረት መዛባትና በሌሎች ምክንያቶች እስከ 500 የሚደርሱት ብቻ ወደ ጫጩትነት እንደሚቀየሩ ገልጸዋል።

የምርምር ማዕከሉም ይህን ችግር ሊቀንስ በሚችል መልኩ በአራቱም ወቅቶች በሰው ሰራሽ ኩሬ አሳ የማምረት ስራ ለማከናወን የሚያስችል እድል መፍጠሩም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በአንድ ሰው ሰራሽ ኩሬ ብቻ ከ10 ሺህ እስከ 12 ሺህ የሚደርስ ዓሳ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በማዕከሉ በሚገኙ 200 የዓሳ ማራቢያ ሰው ሰራሽ ኩሬዎች 100 ሺህ የአሳ ጫጩቶችን በማምረት ዓሳን ማርባት ለሚፈልጉ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዓሳ ማርባት ለሚፈልጉ ዜጎች የአሳ ጫጩት ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ሙያዊ ድጋፍ እየተሰጠ ነው ብለዋል።

የፌደራል የእንስሳት ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ለአሳ እርባታ የሚውሉ ግብዓቶችን በማቅረብና ሌሎች የማስፋፊያ ግንባታዎችን በማካሄድ ለማዕከሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም