ቀጥታ፡

የተጀመረው ለውጥ በስኬት እንዲቀጥል የዴሞክራሲ ተቋማት ሊጠናከሩ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፖለቲካ ለውጥ በስኬት ለማስቀጠል የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር እንዳለባቸው ምሁራን ገለፁ። በአገሪቱ የሚገኙት የዴሞክራሲ ተቋማት ካልተጠናከሩ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ያዳግታል ተብሏል። "የዴሞክራሲያዊ  ሽግግር በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የሁለት ቀናት ሲምፖዚየም ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል። የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ ምሁራን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ በተሳካ መንገድ እንዲቀጥል በተለይ ፍርድ ቤትንና የምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ሊደረግ ይገባል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ፕሮፌሰር እዝቅኤል ገቢሳ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን ፈጣን የፖለቲካ ለውጥ በስኬት ማስቀጠል እንዲቻል ራሱን የቻለ ፍኖተ ካርታ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ አክለውም የዴሞክራሲ ተቋማትን ከማጠናከር ባሻገር እየተካሄደ ባለው ለውጥ ውስጥ ሁለንትናዊ የህዝብ ተሳትፎ የሚጎለብትበት ስርዓት ማበጀትም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት በስነ-ምግባር መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል እርምጃ በፍጥነት መወሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል። “የምርጫና የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ተግዳሮቶችና ዕድሎች” በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሑፍ ያቀረቡት ዶክተር አስናቀ ከፋለ በበኩላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ካልተጠናከሩ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ''ለውጡ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ወሳኝ ነው'' ያሉት ዶክተር አስናቀ ምርጫው ተአማኒና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ እንዳለበትም ገልፀዋል። በዚህ ረገድ የምርጫ ነክ ህጎችና የምርጫ ቦርድ ማሻሻያዎች የማድረግና ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በህጉ መሰረት የመመዝገብ ሂደት ጊዜ ሳይሰጠው ምርጫ ከመድረሱ በፊት መከናወን እንዳለበት ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። ሌላው የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንዳሉት፤ ለውጡ የፈጠራቸውን ተስፋዎች ለማስቀጠል ልዩነቶችን እያስተናገዱና እያጠበቡ በአንድነት መቆም ወሳኝ ነው። በተለይ ለውጡን እየመሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ኃይሎች እርስ በርሳቸው ልዩነቶችን እየፈቱ እርስ በርስ እየተደጋገፉ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። የምርጫ ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልልን፣ ወሰንንና ማንነትን የመሰሉ ጉዳዮችን ለምርጫ ቅስቀሳ በመጠቀም አጀንዳ ባያደርጉ መልካም መሆኑን ምሁራኑ መክረዋል። ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በመማርና ልምድ በመቅሰም መጪው ምርጫ ለውጡን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር እንዲሆን ከወዲሁ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም