ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተሰበሰበበትን የህዳሴ ግድብ ዋንጫ የሲዳማ ክልል ተረከበ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 በኦሮሚያ ክልል በአንድ አመት ቆይታው 1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተሰበሰበበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን የሲዳማ ክልል ተረከበ።

የዘንድሮው  የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት በሀዋሳ ስታዲየም ተከበሯል።

በበዓሉ ላይ በኦሮሚያ ክልል የአንድ አመት ቆይታውን ያጠናቀቀውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን የሲዳማ ክልል በይፋ ተረክቧል።

ዋንጫውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተረክበው ለሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስረክበዋል።  

በመድረኩ እንደተገለጸው፤ ዋንጫው በኦሮሚያ ክልል በቆየበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲሆን ከክልሉ ማህበረሰብ 1 ቢሊዮን 50 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።

የሲዳማ ክልልም ዋንጫው በክልሉ በሚቆይበት በቀጣይ አንድ ዓመት ለህዳሴው ግድብ የሚደረገውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ያከናውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም