ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትሸነፍም በቅርቡ በአዲስ ድል እንደምንገናኝ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትሸነፍም በቅርቡ በአዲስ ድል እንደምንገናኝ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትሸነፍም በቅርቡ በአዲስ ድል እንደምንገናኝ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በሀዋሳ ስታዲየም እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል “ኢትዮጵያ በድምቀትና በሙላት የምትታይበት የኢትዮጵያዊነት ቀን ነው” ብለዋል።
ይህ ዕለት ሁላችንም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆናችንን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን የምናስተምርበት ቀንም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በሰላም የምንኖርበትን ሁኔታ መፍጠር ካልቻልን የምንፈልገውን ልናሳካ አንችልም፣ ሁላችንም በአንድነት የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት መስራት አለብን ብለዋል።
የትላንት ታሪክ መማሪያ እንጂ መወቃቀሻ ሊሆን አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኋላ ታሪክ ላይ በመንተራስ መገፋፋትና መጠላለፍ እንዲቆም አሳስበዋል።
“ኢትዮጵያ ትፈተናለች አንጂ አትሸነፍም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሁን የገጠመን ፈተና ምንም አሳዛኝ ቢሆንም ሀገርንና የነገን ትውልድ መገንባት በሚፈልጉ ዜጎች እናሸንፋለን ኢትዮጵያም ትበለጽጋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በልጽጋ በከፍታ ማማ ላይ ተቀምጣ ለልጆቻችን የምትሻገር መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ ሲሉ አመልክተው ይህንንም በአዲስ ድል በቅርቡ እንደምንገናኝ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ማሸነፍ የሚጀምረው ከእውነትና ፍቅር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእያንዳንዱ አጀንዳ ምላሽ ከመስጠታችሁ በፊት የአጀንዳውን መነሻ ምክንያት በማጣራት መከላከል አለባችሁ ነው ያሉት።
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ከፍታ እውን ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና ያላችሁን ሁሉ ሰጥታችሁ በትጋት እንድትሰሩ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁም ብለዋል።